
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ የነበሩት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ዛሬ አስታውቀዋል፡፡
የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) የሥራ አስፈጻሚ አባልና የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ከኃላፊነት የመልቀቃቸውን ውሳኔ በትግራይ ቴሌቪዥን ገልጸዋል፡፡ የህገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥ የሚለውን ውሳኔ እና ትርጉም ለመሥጠት እየተሄደበት ያለውን መንገድ አለመደገፋቸውን ከኃላፊነታቸው ለመልቀቃቸው በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤነት ስልጣን የመልቀቅ ውሳኔያቸውን አንድምታ አብመድ አስተንትኗል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና የፌደራሊዝም መምህር ሲሳይ መንግስቴ (ዶክተር) ወይዘሮ ኬሪያ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው የቆዩበት ጊዜ አወዛጋቢ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በተለይም ትልቅ ጥያቄ የነበሩትን የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን በአግባቡ ሲመልሱ አልነበረም ብለዋል ዶክተር ሲሳይ፡፡ በዚህ ተግባራቸውም በፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጥያቄውን በሚያቀርቡ ዜጎች ተቃውሞ ሲቀርብባቸው መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ወይዘሮ ኬሪያ በኃላፊነት የቆዩት በድርጅታቸው ግፊት ሳይሆን እንደማይቀር ሀሳብ የሰጡት ዶክተር ሲሳይ አሁን ግን ውሳኔ የሚያስፈልገው ሀገራዊ ጉዳይ ስለመጣ “በኃላፊነት ሆነሽ ውሳኔው ከሚወሰን ኃላፊነቱን ልቀቂና ራሳቸው ይወስኑ” የሚል ሃሳብ ከድርጅታቸው የቀረበላቸው ይመስላልም ብለዋል፡፡ ከኃላፊነት መልቀቃቸውም “ሕወሐት እየለዬለትና እየተሸነፈ እየሄደ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል፡፡ ከኃላፊነት መልቀቃቸውም በፌደሬሽኑ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደማይኖር ነው የተናገሩት፡፡
በተለይም የሕገ መንግሥት ትርጓሜን የማፅደቅ ውሳኔው ላይ በስልጣን ላይ ቢቆዩም ጉዳዩን የበለጠ የመከራከሪያ አጀንዳ ያደርጉት ካልሆነ በስተቀር ውሳኔ የማስቀዬር አቅም እንደማይኖራቸውም ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ የትግራይ ክልል መገናኛ ብዙኃንና ሕወሐት በፌዴራል መንግሥት ላይ የማጥለላት ዘመቻ ከፍተው እየሠሩ መሆኑንም ነው ዶክተር ሲሳይ የተናገሩት፡፡
እንደ ዶክተር ሲሳይ ሀሳብ የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት የሚሰማው፣ የአገሩን መሪ እስከነጉድለቱም ቢሆን ለመቀበል የማይቸገር ነው፡፡ ሕወሐት ግን ሕዝቡ የፌደራል መንግሥት ላይ ጥላቻ እንዲያሳድር ከመሥራት እንደማይቆጠብ ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡