
ሁለተኛውን የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ኤክስፖ ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል።
አዲስ አበባ: ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛውን የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ኤክስፖ ከነሐሴ 24/2017 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ኅብረተሰቡ በንግድ ሳምንቱ እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርቧል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ.ር) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት በንግድ ሳምንቱ 168 የንግድ ድርጅቶች፣ አጋሮች፣ ክልሎች እና የከተማ አሥተዳደሮች ይሳተፋሉ።
የንግድ ሳምንት እና ኤክስፖው ዋና ዓላማ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማስተዋወቅ እና ዜጎች የሀገራቸውን ምርት እንዲገዙ ለማበረታታት መኾኑንም አስታውቀዋል።
የንግድ ሳምንት እና ኤክስፖው የሀገር ውስጥ ምርትን በመጠቀም ዙሪያ የሚስተዋለውን የተዛነፈ አስተሳሰብ ለማስተካከል ግንዛቤ ይፈጠርበታል ነው ያሉት።
ዜጎች በሀገር ምርት የመኩራት ባሕላቸው ይጎለብትበታልም ብለዋል።
ኤክስፖው አምራቾች የሚበረታቱበት እና ለተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚነሳሱበት፣ የሀገር ገቢን ለማሳደግ ሚናው የጎላ መኾኑንም ተናግረዋል።
በመገናኛ የጥራት መንደር በሚካሄደው የንግድ ሳምንት ኤክስፖ ኤግዚቢሽን፣ ባዛር፣ የፓናል ውይይቶች፣ የዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብሮች እንደሚካሄዱበት ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሃመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን