
በ25 ዓመታት ዕቅዱ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ተወዳዳሪ የማዕድን ኢንዱስትሪ መፍጠር ዋነኛ ተግባር ነው።
ባሕር ዳር: ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ አቅዶ ወደ ትግበራ ገብቷል። የትውልድ እና የቁጭት ዕቅዱ የአማራ ክልልን በዘላቂነት ከችግር የሚያወጣ፣ ወደ ተሻለ ዕድገት የሚያደርስ እንደኾነም ተገልጿል።
የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ኀላፊ ሞገስ አያሌው ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ የክልሉን ኢኮኖሚ በፍጥነት አረጋግቶ እንዲያገግም የሚያደርግ ነው ብለዋል። ከዚህ ባሻገር ክልሉን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲያድግ ማድረግ የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የ25 ዓመታት አሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ሳይንሳዊ ዘዴን ተከትሎ የክልሉን ሕዝብ ችግሮች ለይቶ ለችግሮቹ መፍትሔ የሚኾኑ እና ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ መንገዶችን በመለየት መታቀዱን ነው የተናገሩት።
ከ25 ዓመታቱ የአሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ የተቀዳ ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ የሚኾን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ መታቀዱንም ገልጸዋል።
የዕቅዱ መዳረሻ ርዕይ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ አቅም መፍጠር እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ እንደኾነ አንስተዋል። ዋነኛ አላማው ዕቅዱን በአግባቡ በመተግበር ክልሉን ከድህነት ማላቀቅ ብቻ ሳይኾን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲኾን ማስቻል ነው ብለዋል።
ዕቅዱን ውጤታማ ለማድረግ የትናንት ችግሮችን፣ የዛሬ አሁናዊ ሁኔታዎችን፣ የነገ ተስፋ እና ስጋቶችን ሳይንሳዊ በኾነ ትንታኔ በመለየት ማስቀመጡንም አስታውቀዋል።
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሕልውና ጉዳይ መኾኑን ተረድቶ ርብርብ በማድረግ እቅዱን በመፈጸም ድህነትን ታሪክ ማድረግ ይኖርበታል ነው ያሉት።
ዕቅዱ አምስቱን የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ለይቶ ማስቀመጡን የተናገሩት ኀላፊው በዕቅዱ ከተለዩት ዘርፎች አንዱ የማዕድን ዘርፍ መኾኑን ገልጸዋል።
የሰው ልጅ የረጅም ዘመን የሥልጣኔ ለውጥ እና የቴክኖሎጅ መራቀቅ በማዕድናት እና ተያያዥ የከርሰ ምድር ሃብቶች ልማት ላይ የተመሠረተ መኾኑን አንስተዋል። የማዕድን ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የኑሮ መሠረት ከመኾኑ በተጨማሪ በክልሉም ኾነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለዋጋ ማረጋጋት ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ማዕድናት ለማዕድን ኢንዱስትሪ መነሻ አቅም መፈጠር መነሻ ናቸው ያሉት ኀላፊው በሰው ኃይል እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ላይ በመመሥረት ተወዳዳሪ የማዕድን ኢንዱስትሪ ለመፍጠር የሚያግዙ ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠራባቸው ገልጸዋል።
በዚህም የነበሩ አዝጋሚ ለውጦችን በማሳለጥ፣ የዕውቀት፣ የክህሎት እና የአመለካከት ችግሮችን በመቅረፍ የክልሉን ማዕድናት በበቂ እና አስተማማኝ ሁኔታ መለየት ላይ ይሠራል ነው ያሉት። ሃብቱን ለተመረጡ አሻጋሪ ግቦች ጥቅም ላይ በማዋል፣ በዘርፉ የሚሠማሩ ባለሀብቶችን እና የሚፈሰውን መዋዕለ ንዋይ ከፍ በማድረግ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በመጠቀም በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የክልሉን እና የሀገር ውስጥ ማዕድናትን ለዘመናዊ ግብርና ልማት ማዋል፤ በማዕድን ሃብት ልማት ዘላቂ ማኅበረሰባዊ፣ ክልላዊ እና ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፤ የማዕድን ዓይነት፣ ጥራት፣ ክምችትን እና ሥርጭትን ለስትራቴጂካዊ ማዕድናት ቅድሚያ ሰጥቶ በጥናት ማረጋገጥ በዋናነት የሚተገበሩ እንደኾኑ ተናግረዋል።
በሰው ኃይል እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ተወዳዳሪ የማዕድን ኢንዱስትሪ መፍጠር የስትራቴጅክ ዕቅዱ ዋና ተግባራትም ናቸው ብለዋል።
ይህን ውጤታማ ለማድረግ የሠለጠነ የሰው ኃይል መፍጠርም ይኖርብናል ነው ያሉት። የአሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅዱን በተሳካ ሁኔታ መፈጸም ከተቻለ ክልሉ አሁን ካለበት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ተላቆ ወደ ብልጽግና መሸጋገር ይቻላል ብለዋል።
ዕቅዱ እስካሁን በክልልም ኾነ በሀገር ደረጃ በአይነቱ ልዩ የኾነ እና ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ የተዘጋጀ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!