
ጎንደር: ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሻደይ አሸንድየ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ ተከብሯል።
የበዓሉ ማጠቃለያ መርሐ ግብር “ባሕላዊ እሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተከበረው።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ እና የባሕል እሴት ባለሙያ ትዕግስት ካሳየ የሻደይ አሸንድየ በዓል በዞኑ በሚገኙ አራት ወረዳዎች ሲከበር መቆየቱን ተናግረዋል።
በዓሉ ከነሐሴ 16/2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲከበር መቆየቱን አንስተው ዛሬ ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመቀናጀት የማጠቃለያ መርሐ ግብር መካሄዱን አስታውቀዋል።
በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ መስተጋብር ያለው መኾኑን ያነሱት ተወካይ ኀላፊዋ አንድነትን እና አብሮነትን ለማጠናከር ብሎም ባሕልን ለመጠበቅ የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የትያትር ጥበባት ባለሙያ መንጌ መልካሙ በበኩላቸው የሻደይ አሸንድየ በዓል ዕሴቱን በጠበቀ መልኩ ተከብሯል ብለዋል።
ባሕላዊ እሴቶች ለሰላም እና ለአብሮነት ሚናቸው ከፍ ያለ መኾኑንም አንስተዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በዓሉን ለማክበር ቀድመው ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ነግረውናል።
በዓሉ ለሴት ልጆች የነፃነት እና የአብሮነት በዓል ስለመኾኑም ተሳታፊዎቹ አስታውሰዋል።
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋ