
ደባርቅ: ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ350 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ታደሰ ሙሃባው እንደገለጹት በዞኑ በሚገኙ አካባቢዎች የንቅናቄ መድረክ ሲካሄድ ቆይቷል።
በመድረኮችም ከትምህርት ባለ ድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዶ የጋራ አቋም መፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል።
በትምህርት ዘመኑ ስኬታማ የመማር ማስተማር ሥራ ለመከዎን የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
የመምህራን የሥራ ስምሪት፣ የትምህርት ቤት ጥገና እና የትምህርት ዕቅድ ዝግጅ ክለሳ ከተከናዎኑ ተግባራት መካከል እንደሚጠቀሱ አብራርተዋል።
አቶ ታደሰ ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም የአንድ ጀምበር የተማሪዎች ምዝገባ በተሳካ ሁኔታም ተከናውኗል ብለዋል።
ከነሐሴ 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የተማሪዎች ምዝገባ ሥራ እየተከናዎነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የደባርቅ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈረደ ይትባረክ በበኩላቸው በትምህርት ዘመኑ በከተማ አሥተዳደሩ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የምዝገባ ሥራው ቀደም ብሎ መጀመሩ የትምህርት መርሐ ግብሩ በታቀደው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲከናዎን እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በደባርቅ ዋልያ ትምህርት ቤት አሚኮ ተገኝቶ ያነጋገራቸው ተማሪዎች የምዝገባ ሥራ እየተከናዎነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ምዝገባው ቀደም ብሎ መጀመሩ የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት እና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችን ለማድረግ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም የተማሪዎች ምዝገባ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለ ድርሻ አካል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋ