
ባሕር ዳር: ነሐሴ 2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የ30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የማጠቃለያ ዝግጅት እየተካሄደ ነው።
በማጠቃለያ ዝግጅቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የርእሰ መሥተዳድሩ የሕዝብ ግንኙነት እና አደረጃጀት አማካሪ እና የአሚኮ የሥራ አመራር ቦርድ ሠብሣቢ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በማጠቃለያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላልፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሚኮ ሕዝብን ማዕከል በማድረግ ሀገርን በመገንባት፣ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ድልድይ በመኾን፣ ዕውነትን በዕውቀት ይዞ ሲያገለግል ኖሯል ነው ያሉት።
አሚኮ በግጭትም በሰላምም ኾኖ ለሀገር እና ሕዝብ ዕውነተኛ የመረጃ ምንጭ የኾነ እና ለሀገር ሁነኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ነው ብለዋል። ዛሬ የ30 ዓመታት የምሥረታ በዓል የምናከብረው የወደፊት ርዕዩን እንዲያሳካ መሠረት ለመጣል ነውም ብለዋል።
አሚኮ የተመሠረተው የሚዲያ ምኅዳሩ ጠባብ በነበረበት እና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ባልነበረበት ወቅት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በዝቅተኛ የቴክኖሎጂ ተነስቶ እዚህ የደረሰ ታላቅ ተቋም መኾኑን ገልጸዋል። አሚኮ ትልቁ ሀብቱ ርዕዩ እና ቁርጠኝነቱ ነው ብለዋል። በቁርጠኝነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፣ የሕዝብን ትስስር እና የሀገርን አንድነት ለማጠናከር ሠርቷል ነው ያሉት።
አሚኮ የሕዝብን ትስስር ለማጠናከር እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በዚህም ሥራው በብዙዎች ይወደዳል፣ ጫፍ የረገጡ አካላት ደግሞ ይጠሉታል ብለዋል። ግጭት በውይይት እንዲፈታ መሥራቱንም ተናግረዋል። በግጭት ወቅት ሁሉም በሚደናገርበት ጊዜ ዕውነትን መሠረት አድርጎ በጽናት እና በቁርጠኝነት መሥራቱንም ገልጸዋል።
አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት እምነት የሚጣልበት ተቋም ኾኖ ሠርቷል ነው ያሉት። አሚኮ ለሀገር እና ሕዝብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ በብዙ ውጣውረዶች አልፏል ብለዋል። አሚኮ ፈተናዎች ሳይበግሩት ተወዳዳሪ ኾኖ ለመውጣት የሠራ ሚዲያ መኾኑን ገልጸዋል።
የአሚኮ መሪዎች እና ሠራተኞች በአካል የሚደርስን ጥቃት ጭምር በመቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት። አሚኮ በክልሉ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የምንመለከተው ተቋማችን ነው ብለዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በችግር ውስጥ ኾኖ የሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የሀሰተኛ መረጃዎች መብዛት ያልበገሩት ዕውነትን ይዞ የወጣ ነው ብለዋል።
“አሚኮ የሕዝባችን ጠንካራ ተቋም ብቻ ሳይኾን ልዩ ምልክቱ ኾኖ እየቀጠለ ነው” ብለዋል። የቀጣይ መዳረሻው የተጠናከረ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ወደፊት ራሱን በቴክኖሎጂ እያበቃ፣ ሕዝብን እያስተሳሰረ፣ ለምንፈልጋት ሀገር አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እንፈልጋለን ነው ያሉት።
ዕውነትን ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ለሕዝብ እንዲያደርስ እንደሚፈለግም ገልጸዋል። አሚኮ ተደራሽነቱን እያሰፋ መሄዱንም ተናግረዋል። አሚኮን አሁን ካለበት የበለጠ ማስፋት እና ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል። አሚኮን እዚህ ላደረሱ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
አሚኮ ራሱን ያሳድጋል፣ ያሰፋል፣ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ዕውነትን ያደርሳል፣ ሕዝባችንን ያስተሳስራል፣ ሀገራችንን ያሳድጋል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን