
አዲስ አበባ: ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የመንገድ ዘርፍ 2ኛ ጉባኤ “ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ” በሚል መሪ መልዕክት የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ መንገድ ፈጣን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት ሚናው የጓላ ነው ብለዋል። የመንገድ አውታር ከተማን ከከተማ እና ከተማን ከገጠር በማገናኘት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥርን እያሳደገ ነው ብለዋል። በመንግሥት የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ትኩረት ከተሠጣቸው የልማት ዘርፎች የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ አንዱ ነው። በዚህም የሀገሪቱ የመንገድ አውታር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የሕዝቡን የመንገድ ይገንባልን ጥያቄ ለመፍታት በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር 101 ቢሊዮን ብር በመመደብ ከ1 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው አዳዲስ መንገዶችን መገንባት ተችሏል ነው ያሉት። ከ10 ሺህ 900 ኪሎ ሜትር በላይ ነባር መንገዶችን በመደበኛ መጠገን መቻሉንም አንስተዋል። መንግሥት ለእነዚህ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ማፍሰሱን ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት። በመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ መኾኑንም ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ አረጋግጠዋል። እንደ ሀገር አሁን ላይ ያለው የመንገድ አውታር በቂ አለመኾኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ የዜጎችን የመንገድ ፍላጎት ለማሟላት ግንባታዎችን በታሰበላቸው ጊዜ እና በጀት ማጠናቀቅ ይገባል ብለዋል።
አዳዲስ መንገዶችን ከመጀመር በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያቶች የተቋረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜ ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ በየዘርፉ ያሉ የሥራ ኀላፊዎች ትኩረት ሠጥተው እንዲሠሩም ሚኒስትሯ አሳስበዋል። በጉባዔው የተገኙት የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ምስጦፌ መሐመድ መንገድ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የማይተካ ሚና እንዳለው አንስተዋል። በሱማሌ ክልል ከለውጡ በኋላ ጥራት እና ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት የክልሉን ሕዝብ የመንገድ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የዜጎችን ማኅበራዊ ትሥሥር እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። አሁን ያለውን የመንገድ ሽፋን ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ከፍ ያለ መኾኑን ጠቁመዋል። ክልሉን ከሌሎች ከተሞች ጋር በማስተሳሰር ማኅበራዊ ግንኙነቱ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው የተሳለጠ እንዲኾን በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን