
ገንዳ ውኃ፡ ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን በ2018 የትምህርት ዘመን ከ146 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዝግጅት ማጠናቀቁን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደሳለኝ አያና ተናግረዋል።
የጸጥታ ችግር ካለባቸው ትምህርት ቤቶች በስተቀር በሁሉም ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ ተጀምሯል ነው ያሉት።
ተማሪዎችን ምቹ በኾነ የመማሪያ ክፍል ለማስተማር በዞኑ ከ55 በላይ የመማሪያ ክፍሎች በብሎኬት መገባቱን ገልጸዋል። በጊዜያዊነት ለማስተማሪያ ተብሎ ከ80 በላይ የእንጨት የመማሪያ ክፍሎች እንደተሠሩም አብራርተዋል።
ይህም ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የመማር ማስተማሩን ሂደት ያሳልጠዋል ነው ያሉት።
ሌሎች የግብዓት ችግሮችን ለመቅረፍም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቃሲም አብዴ በበጀት ዓመቱ ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግበን ለማስተማር አቅደናል ነው ያሉት።
ዕቅዱን ለማሳካትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ቅስቀሳ አድርገው ዛሬ ምዝገባ እንዳስጀመሩ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በቁሳቁስ ምክንያት ያቋረጡ ተማሪዎች በአዲሱ ዓመት እንዳያቋርጡ በርካታ ሥራዎች እንደተሠሩ እና ለተማሪዎች ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አስረድተዋል።
ትምህርት ቤቶችን ከምዝገባ ጀምሮ ትምህርት እስኪጠናቀቅ ድረስ በአካል በመገኘት እና የድጋፍ ባለሙያ በመላክ ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ሁሉም ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለምዝግባ እንዲልኩም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ የቁጥር ሁለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር አብራራው ሰጥአርጌ እና መምህርት አደይ አሰማው ተማሪዎች በጊዜ ሰሌዳው መሠረት እንዲመዘገቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን ቅስቀሳ አድርገናል ነው ያሉት።
ለመማር ማስተማሩ ሥራ ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የቀጣዩ የትምህርት ዘመን ሥራ ጥራት ያለው እንዲኾን እና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት።
የ8ኛ እና የ7ኛ ክፍል ተማሪዎች መላኩ ሃብቴ እና መክሊት ሰለሞን ቀድሞ ምዝገባ በመጀመሩ ደስተኛ መኾናቸውን ነግረውናል።
ከዚህ በፊት ዘግይቶ ምዝገባ እና ትምህርት ስለሚጀመር ትምህርቶች ሳያልቁ ነው ሚቀሩት፣ አሁን ግን ቶሎ መጀመሩ በጊዜ እንዲያቁ ይረዳል ብለዋል።
ለአዲሱ የትምህርት ዘመንም በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ እና ለመማር ፍላጎታቸው ከፍተኛ እንደኾነም አስረድተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!