
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “አሚኮ በ30 ዓመታት ጉዞው ውስጥ ዘመን የደረሰባቸውን የመረጃ እና ተግባቦት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተደራሽነቱን ከጥራት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ጋር አስተሳስሮ ዛሬ ላይ የደረሰ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡
ተቋሙ ከሕትመት፣ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ባሻገር የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን እየተጠቀመ የመረጃ ቴክኖሎጂ ዘመንን እየዋጀ ይገኛል፡፡
የማኅበራዊ ትስስር አማራጮች የሚዲያ ኢንዱስትው ላይ የመረጃ ሥርጭትን በማፍጠን፣ ተሳትፎን በማጎልበት፣ ቀልጣፋ አማራጭ በመኾን፣ አሁናዊ (real-time) የታዳሚ ግብረ መልስ ማግኛ በመኾን እና የገቢ ምንጭም ጭምር በመኾን የዓለምን ሕዝብ ድንበር አልባ ግንኙነት እንዲያደርግ የሚያግዝ የዘመኑ ውጤት ነው፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያን በጎ ዓላማ ቀድሞ በመረዳት አሚኮ በ2005 ዓ.ም ኦንላይን እና ሞኒተሪንግ በሚል ቡድን ተዋቅሮ በቴሌቪዥን ዝግጅት ክፍል ስር ኾኖ በጥቂት ሰዎች ነው ሥራ የጀመረው፡፡ ሥራዎች የተጀመሩትም በፌስቡክ ነበር። በ2008 ዓ.ም ደግሞ በራስ አቅም በለማ ድረ ገጽ ሥራውን እያሳደገም መምጣት የቻለ ነው።
በአሚኮ የነበረውን የዲጂታል ሚዲያ ጉዞ በተመለከተ ያነጋገርናቸው በአሁኑ መጠሪያው የዲጂታል ሚዲያ ክፍል ዳይሬክተር የኾኑት መላኩ ሙሉጌታ የማኅበራዊ ሚዲያ ሥራው እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ራሱን ችሎ አልተደራጀም ነበር ብለዋል፡፡ ከ2010 ዓ.ም በኋላ ግን ራሱን ችሎ በዳይሬክተር ደረጃ እየተመራ የዩቲዩብ ቻናልን ከፍቶ የይዘት ተደራሽነቱን በቪዲዮ አማራጭ ጭምርም አሳድጓል ብለዋል፡፡
በጣም ፈጣን በኾነው የመረጃ እና ተግባቦት የቴክኖሎጂ ጉዞ ውስጥ ራስን እያላመዱ መሄድ ግድ የሚል በመኾኑ አሚኮ በ2013 ዓ.ም የማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ቁሳቁስ፣ በሰው ሃብት እና በአደረጃጀት በአዲስ መልክ አዋቅሮ “ዲጂታል ሚዲያ” በሚል መጠሪያ አዲስ ቀለም ይዞ ተከስቷል ነው ያሉት አቶ መላኩ፡፡
ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተደራሽ ከመኾን ባሻገር አሚኮ በክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ አስተዋጽኦን በማበርከት ረገድ የላቀ ሚናን ተጫውቷል ብለዋል፡ የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ አደረጃጀቱን፣ የሰው ሃብቱን እና የሚዲያ አማራጩን እያሰፋ በሂደት እያደገ የመጣ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በዲጂታል ሚዲያ ክፍል የሚሠሩ የኦንላይን ሥርጭት አገልግሎቶች ከተቋሙ ውጭ ባሉ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ይከናወን እንደነበር እና ይህ ደግሞ ለተጨማሪ ወጭ የሚዳርግ ከመኾኑም በላይ የጥራት ችግሮችም ስለነበሩበት የራስን የቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ በዩቲዩብ፣ በፌስቡክ፣ በቲክቶክ እና በቴሌግራም ቀጥታ ሥርጭት ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ በቴሌቪዥን የሚሠሩ ዘገባዎች ለዲጂታል ሚዲያ በሚኾን መልኩ ቆርጦ ለመሥራት (Content Repurposing) ጥራት ያለው የኦንላይን ቅጅ (Recording) ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
ዲጂታል ሚዲያ ለአሚኮ ተደራሽነትን ከፍጥነት ጋር አስተሳስሮ ለማስፋት ከማገዝም በላይ የገቢ አማራጭም መኾን የቻለ ነው ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በዩቲዩብ እስከ 48 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወራዊ ገቢ የተገኘበት ጊዜ መኖሩንም አስታውሰዋል፡፡
የተለያዩ ዘመኑ የደረሰባቸውን ሶፍትዌሮችን በመጠቀም የኢንፎግራፊክስ እና ቪዲዮ ዘገባዎችን በመሥራት እና በማኅበራዊ ሚዲያ ተደራሽ እንዲኾኑ በማድረግ አማራጮችን ማስፋት መቻሉን እና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለዘገባ ሥራ እንደ ቅመም አድርጎ በመጠቀም ቀዳሚ መኾን ችለናል ብለዋል፡፡ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዘጋጀ ዘገባን ቀድሞ በማላመድ እና በመጠቀም በአፍሪካ ሁለተኛ እና በኢትዮጵያ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።
አቶ መላኩ የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ በጣም ጠንካራ፣ ጥልቀት ያላቸው እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የቴክስት እና የቪዲዮ ዘገባዎችን በመሥራት፤ የአሁኑን ዘመን የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚዎች ግምት ውስጥ ያስገባ ከፍ ያለ ሥራ እየሠራን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡ ከዲጂታል ሚዲያ ቴክኖሎጂ በተጨማሪ አሚኮ በርካታ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በመሥራትም የስርጭት አድማሱን አስፍቷል ነው ያሉት፡፡
ከዋናው የቴሌቪዥን ቻናል በተጨማሪ የኅብር ቻናል ሥርጭቱ በኢንተርኔት አማካኝነት ወደ ሳተላይት እንዲደርስ እና እንዲሰራጭ ማድረግ መቻሉን እና ከሰባት በላይ በሚኾኑ ቦታዎች ላይ የተለያዩ የቀጥታ ሥርጭቶችን ማድረግ የሚያስችሉ የዲ.ኤም.ኤን.ጂ ቴክኖሎጂዎችንም አገልግሎት ላይ እየዋሉ መኾኑን የነገሩን ደግሞ በአሚኮ የመረጃ ቴክኖሎጂ እና ሚዲያ አገልግሎት ዳይሬክተሩ አቶ ታምር ታከለ ናቸው፡፡
የቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ፋይሎች በሰርቨር ተሳስረው በቀላሉ የሚገኙበት መንገድ ተግባራዊ መደረጉ፣ ከቅርንጫፎች ጋራ ተቋማዊ በኾነ የመረጃ መረብ በተሳሰረ ሥርዓት (VPN) የቀጥታ ሥርጭት መምራት የሚቻልባቸው ሥራዓቶች መፈጠራቸው፣ በራስ አቅም የለሙ እና ቁልፍ ተግባራትን የሚያከናውኑ ሶፍትዌሮችን ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉ የአሚኮን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ማሳያዎች እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡
አሚኮ ካሉት እጅግ ዘመናዊ የኾኑ መገልገያዎች ውስጥ በሮቦት የሚሥራ የቪዲዮ ፋይሎችን እያደራጀ ለሰርቨር ሥርዓቱ የሚመግብ ቴክኖሎጂ አንዱ መኾኑን እና ቁልፍ ተግባራትን እያሳለጠ እንደሚገኝም አቶ ታምር ገልጸዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!