
ከሚሴ: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሁሉም ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች ትምህርት ቤቶች ላይ የተማሪዎች ምዝገባ በንቅናቄ ተጀምሯል።
በደዋጨፋ ወረዳ የቆላዲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር አልማዝ ሰይድ በ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ለመመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው ለስኬቱ በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል። የደዋ ጨፋ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ አሕመድ አብዱ አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ እንዳይቀር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መደረጉን ገልጸው በፓይለት የምዝገባ ሥራውም 74 በመቶ ምዝገባ መካሄዱን ጠቁመዋል። በወረዳው ባሉ 65 ትምህርት ቤቶች ከ46 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የደዋጨፋ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ እና የማኅበራዊ ክላስተር አሥተባባሪ አሕመድ ሀሰን በወረዳው አንድም ተማሪ ከትምህርት ውጭ እንዳይኾን በቁጭት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል። በትምህርት ቁሳቁስ ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት እንዳይስተጓጎሉ በወረዳው የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እየተሠበሠበ መኾኑንም አሥረድተዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ሙክታር እንድሪስ ከዚህ ቀደም በተካሄደው የፓይለት ምዝገባ በ23 ትምህርት ቤቶች ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መመዝገብ እንደተቻለ ጠቅሰዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ217ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሠራ ነውም ብለዋል። በተማሪዎች ምዝገባ ወቅት የማኅበረሰቡ ተሳትፎ የላቀ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን