
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የ30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ዐውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።
በዐውደ ጥናቱ “ብሔራዊ ጥቅም እና የሚዲያ ሚና” በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ.ር) ሀገር ለአንድ ዜጋ ወሳኝ ሃብት ነው ብለዋል። ሀገር የሌለው ምንም ቢኖረው ዋጋ የለውም ነው ያሉት። አንድ ሀገር ሕዝብ፣ ድንበር፣ መንግሥት እና ሉዓላዊነት ሊኖሩት እንደሚገባ ገልጸዋል። ሀገር ያለ ብሔራዊ ጥቅም መኖር አትችልም ያሉት ሚኒስትሩ ሚዲያዎች የብሔራዊ ጥቅም ማስከበሪያ መንገዶች ናቸው ብለዋል። ብሔራዊ ጥቅም የሀገርን ሕልውና፣ ደኅንነት፣ ብልጽግና እና ተጽዕኖ ማስቀጠል እንደኾነ ተናግረዋል። ሀገራት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር አሉ የሚሏቸውን አማራጮች ሁሉ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።
የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ የአንድ ግለሰብ፣ የአንድ መንግሥት ወይም ፓርቲ ጉዳይ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ብሔራዊ ጥቅም የአንድ ሀገር እና ሕዝብ አጀንዳ እና ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል። ብሔራዊ ጥቅም ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር መኾኑንም በመጨመር። የሀገራዊ ሕልውና ደኅንነት፣ የግዛት አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ነጻነት መረጋገጥ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ፣ ራስን መቻል፣ ከድህነት መውጣት፣ መበልጸግ፣ ፖለቲካዊ አቅም እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት፣ የባሕል ነጻነት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና የሕዝቦች ማኅበራዊ ልማት መረጋገጥ የብሔራዊ ጥቅም መሠረታዊ ግቦች መኾናቸውን አንስተዋል።
ዛሬ ላይ ትምህርት ቤቶችን የሚዘጋ የትኛውም ኀይል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የመጣ መኾኑን ገልጸዋል። ያላወቀ ትውልድ ነገ ሀገሩን አሳልፎ እንደሚሰጥም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በጂኦ ስትራቴጂካዊ ጉዳይ ታላቅ ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሩ በሁሉም መለኪያ ታላቅ ሀገር መኾኗን አመላክተዋል። ኢትዮጵያ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም አውቀን መሥራት ከቻልን ኢትዮጵያን የበለጸገች እናደርጋታለን ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿ ጉዳት ሲደርስባቸው እንደኖሩም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ያልተገራ ፍላጎት፣ ባንዳዎች ለዘመናት ለታሪካዊ ጠላቶች ማደር፣ የኢትዮጵያ ጂኦ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታው አለመጠናቀቅ፣ ደህነት እና ኀላቀርነት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች የብሔራዊ ጥቅሞቿ ዋነኛ ፈተናዎች መኾናቸውን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ፈተና የኾኑ ጉዳዮችን መፍታት እንደሚገባ አመላክተዋል። ሰላም ማጣት እና ድህነት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲሰናከል እና በዓለም ላይ የሚገባትን እንዳታገኝ ማድረጉን ገልጸዋል። ለብሔራዊ ጥቅም መረጋገጥ ውስጣዊ አንድነትን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል። ውስጣዊ አንድነቱን ያላረጋገጠ ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅምን እንደማያረጋግጥ አመላክተዋል። ለብሔራዊ ጥቅም መረጋገጥ ሰላም እና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ባሕልን ማዘመን እና የሃሳብ ፖለቲካን ማስፈን፣ ከፖለቲካ ኀይሎች ጋር ሰላማዊ አማራጭ መከተል፣ ሀገራዊ መግባት መፍጠር፣ የጋራ ትርክትን በጋራ ጥቅም ላይ መገንባት እንደሚገባም አንስተዋል። የምጣኔ ሃብታዊ አቅምን ማሳደግ ብሔራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል። የሚለምን ሀገር እና ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ እንደማይቻለው አንስተዋል። ከድህነት ነጻ የኾነ ትውልድ መፍጠር የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን የሚያረጋግጥ የዲፕሎማሲያዊ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም አንስተዋል። የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ያደረገ ሚዲያ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የሚዲያዎች አጀንዳ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ሊኾን እንደሚገባ አመላክተዋል። አሚኮ ሀገርን እየገነባ 30 ዓመታት ላይ ደርሷል ያሉት ሚኒስትሩ ብሔራዊ ጥቅም ላይ መሥራቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አመላክተዋል። ሚዲያዎች ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ፣ ሀገራዊ ስኬትን እና ድልን የሚያጎሉ፣ በብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ግንዛቤ የሚፈጥሩ፣ ኢትዮጵያውያንን ለብሔራዊ ጥቅም የሚያሠባሥቡ እና የሚያታግሉ፣ የሚዲያ ይዘቶችን ሁሉ በሀገራዊ ጥቅም ዕይታ የሚቃኙ እና ሀገራዊ ተጋላጭነትን የሚቀንሱ አጀንዳዎችን መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ጠላቶችን ፍላጎት የሚያመክኑ፣ ሀገራዊ ትርክቶችን የሚገነቡ፣ ሀገራዊ ገጽታን የሚገነቡ አጀንዳዎችን መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። የብዝኀ ሚዲያ ስትራቴጂን መከተል፣ ለዲጂታል ሚዲያ እና ለዲፕሎማሲ ልዩ ትኩረት መስጠት፣ የብዝኃ ቋንቋ ስትራቴጂን መተግበር፣ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ በአጀንዳ ላይ የመቆየት እና የማስረጽ ስትራቴጂን መከተል፣ ኃይል የሚያሠባሥብ እና ወዳጅ የሚያበዛን ስትራቴጂ መከተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። መላው ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ አንድ መኾን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። ሚዲያዎች ብሔራዊ ጥቅምን ቁልፍ አጀንዳ አድርገው መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የሚዲያዎች አጀንዳዎቻቸው እና መልዕክቶቻቸው በብሔራዊ ጥቅም የተቃኙ እንዲኾኑም ገልጸዋል። ይህን ሲያደርጉ በሀገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችልም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን