ምዝገባ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

9
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች በጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ፣ ጠይማ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ እንዲሁም በወተት በር የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤቶች ተገኝተው የምዝገባ ሂደቱን ተመልክተዋል።
በጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለምዝገባ ያገኘናት የ12 ኛ ክፍል ተማሪዋ ኤፍራታ ዘላለም ክረምቱን በግሏ የቋንቋ ትምህርት በመማር፣ የ12ኛ ክፍል መማሪያ እና እጋዥ መጽሐፍትን በማንበብ ማሳለፉን ነግራናለች። አሁን ላይም ቀድማ ተመዝግባለች። በቀጣይ የሚሰጡ ትምህርቶችን በመከታተል እና በወቅቱ በማንበብ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እያደረገች መኾኗን ገልጻልናለች። ከዚህ በፊት በጸጥታው ችግር ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ምኞቷንም ገልጻለች።
በጠይማ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጃቸውን ለማስመዝገብ ያገኘናቸው ወርቁ አስረስ ትምህርት ቤቶች በጊዜ የተገደቡ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በመኾናቸው ወላጆች በወቅቱ ልጆቻቸውን ሊያስመዘግቡ ይገባል ብለዋል። ከምዝገባ በኋላም በወቅቱ ግብዓት በማሟላት ትምህርት እንዲጀምሩ ማድረግ እንዳለባቸውም መክረዋል። በ2018 የትምህርት ዘመን ውጤታማ ሥራ መሥራት ከተፈለገ ወላጆች፣ የትምህርት ባለሙያዎች እና የመንግሥት ተቋማት በተቀናጀ መንገድ ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
የጠይማ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሙሉጌታ ባለው ከክረምቱ ወራት ጀምሮ ትምህርት ቤቱን የማስዋብ፣ የተጨማሪ ክፍሎች ግንባታ፣ ግብዓት የማሟላት እና የጥገና ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸውልናል። በትምህርት ዘመኑም 2 ሺህ 799 ተማሪዎችን ለማስተማር የምዝገባ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። የትምህርት ባለሙያዎችም ዝግጁ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ ከዚህ በፊት በክልሉ በሙከራ ደረጃ ምዝገባ ሲካሄድ ቆይቷል ብለዋል። ውጤታማ ምዝገባ ያካሄዱ እንዳሉ ሁሉ በሂደት ላይ ያሉ መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ዛሬ በሙከራ ደረጃ የታዩ ውስንነቶችን በማረም በክልል ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚገኙ ተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል ነው ያሉት። 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎችም ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። በተደራጀ መንገድ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማከናወን ሁሉም አካል የምዝገባ ሂደቱን እንዲያግዝ ጠይቀዋል። ተማሪዎች ከተመዘገቡ በኋላም ወላጆች አስፈላጊ የትምህርት ግብዓቶችን አሟልተው ከትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ የማድረግ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአጭር ጊዜ የተማሪዎችን ምዝገባ ለማጠናቀቅ እየሠራ መኾኑን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።
Next article“ለብሔራዊ ጥቅም መረጋገጥ ውስጣዊ አንድነትን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው” ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ.ር)