
ሰቆጣ: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ መሥተዳድሮች የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባ ተጀምሯል።
ከትምህርት መምሪያው የተውጣጡ መሪዎችም በሰቆጣ ዙርያ ወረዳ ሐሙሲት ከተማ ተገኝተው የተማሪዎች ምዝገባ ተመልክተዋል። ተማሪ እሸቱ ጌታየ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሲኾን በሰዓቱ በመመዝገቡ ለትምህርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እንዲያሟላ እና በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ እንደሚረዳው ተናግሯል።
በዓድዋ ድል አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪዋ ሄቨን በሪሁን ክረምቱን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭ ተማሪዎች ትምህርቷን ስትከታተል እንደነበረች ገልጻለች። በቀጣይም የተሻለ ደረጃ ለመያዝ ቀድሞ ከመመዝገብ ጀምሮ አስፈላጊውን የመማሪያ ቁሳቁሶችን እንዳሟላች ነግራናለች። ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲኾኑ የወላጆች ሚና አስፈላጊ መኾኑን የነገሩን ደግሞ ልጃቸውን ሲያስመዘግቡ ያገኘናቸው ወይዘሮ አበባ አስፋው ናቸው።
ለልጃቸውም አስፈላጊውን ግብዓት እንዳሟሉ የገለጹት ወይዘሮ አበባ ሌሎች ወላጆችም በሰዓቱ ልጆቻቸውን እንዲያስመዘግቡ አሳስበዋል።
በሰቆጣ ዙርያ ወረዳ በ2018 ዓ.ም በሁሉም የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅደው እየሠሩ መኾናቸውንም የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ብርሃኑ ዘገየ ገልጸዋል። በክረምቱ ወቅትም ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር የንቅናቄ መድረክ እንዳካሄዱ የጠቆሙት ምክትል ኀላፊው የተማሪ ምዝገባንም በንቅናቄ እና በአደረጃጀት መጀመሩን ተናግረዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሁሉም ወዳዎች እና ከተማ መሥተዳድሮች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተማሪ ምዝገባ መጀመሩን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ፍታለሽ ምህረቴ ገልጸዋል። በ2018 ዓ.ም በዋግ ኽምራ ከ260 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሠራ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊዋ ለዚህም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቅቆ ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል። የተማሪ ምዝገባ ከነሐሴ 19/2017 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም ድረስ ቢኾንም በአጭር ጊዜ ምዝገባውን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ያሉት ወይዘሮ ፍታለሽ የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸውን በሰዓቱ እንዲያስመዘግቡም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን