
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የ30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።
በአውደ ጥናቱ ላይ “የቀውስ ወቅት እና የሚዲያ ሚና” በሚል ርእሰ ጥናት ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን መምህር እና ተመራማሪ ጀማል መሐመድ (ዶ.ር) ቀውስ የሚባለው ለሰዎች ያልተመቸ ሁኔታ ሲፈጠር ነው ብለዋል። ቀውስ አካባቢያዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌላ ሊኾን እንደሚችል ነው የተናገሩት። ቀውስ ድንገት የሚፈጠር “የብራ መብረቅ” አይደለም የሚሉት ምሁሩ ቀውስ ቀስ በቀስ እንደሚመጣ ገልጸዋል። ቀውስ ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮች አስቀድመው ይፈጠራሉ፣ ቀውስ እንዳይመጣ ምልክቶቹን በመመልከት አስቀድሞ መሥራት ደግሞ ቀውስን ያስቀራል ነው ያሉት።
ሚዲያ በቀውስ ወቅት የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባው አንስተዋል። ሚዲያን በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ ቀውስን ሊያባብስ እንደሚችልም ገልጸዋል። በተለይም በዚህ ዘመን ሃሰተኛ መረጃዎች የሚስፋፉበት ቴክኖሎጂ እንደተፈጠረ ነው የተናገሩት። ሚዲያን በትክክል መጠቀም ከተቻለ እና ማኅበራዊ ኀላፊነት የሚሰማው ሚዲያ ከኾነ ቀውስን ወደ ውይይት ማምጣት እንደሚቻል አንስተዋል። በቀውስ ወቅት ሚደያዎች ውይይት እንዲፈጠር እና ችግሩ እንዲፈታ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። ሚዲያዎች ማኅበራዊ ኀላፊነት ሲሰማቸው ሰላምን ማጉላት እንደሚችሉም ተናግረዋል።
በቀውስ ወቅት የሚዲያዎች የቋንቋ አጠቃቀም ትልቅ ትርጉም እንዳለው የገለጹት ምሁሩ የቋንቋ አጠቃቀም ሰላምን ሊያመጣም፤ ቀውስን ሊያባብስም እንደሚችል ነው ያመላከቱት። በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያው ኾነ ብለው መረጃን የሚያዛቡ እና ሳያውቁ ደግሞ የሚያሳስቱ እንዳሉ አንስተዋል። ሚዲያን ላልተገባ ዓላማ መጠቀም አደጋው ከባድ መኾኑንም ገልጸዋል። “አንድ ሕዝብ ከአንድ ታላቅ ሚዲያ የሚጠብቀው የሀገር ሰላምን መኾን እንዲነግረው ነው” ብለዋል። ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃን በአግባቡ ማቅረብ እንደሚገባ የተናገሩት ምሁሩ ዘመኑ መረጃን ለማዘግየት እና ለመደበቅ እንደማይኾን ተናግረዋል።
ሚዲያዎች ሰዎች ውይይትን እንዲመርጡ ማመቻቸት፣ ግጭትን በውይይት የመፍታት ባሕል እንዲዳብር መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። መግባባት የሚፈጠረው በውይይት መኾኑንም ተናግረዋል። ሚዲያዎች በቀውስ ወቅት በብዙ መንገድ እንደሚፈተኑም አንስተዋል። በቀውስ ወቅት የሚፈጠረውን ችግር ለመፍታት ቀውስ ከመምጣቱ በፊት አስቀድሞ መዘጋጀት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። ሚዲያዎች የሚሠሩብትን መንገድ አስቀድመው ሲዘጋጁ ቀውስን ለማረጋጋት ይችላሉ ነው ያሉት።
የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፉ ውይይት ነው ያሉት ምሁሩ ውይይት ቶሎ መፍትሔ ባያመጣ እንኳን በውይይት ሰው አይሞትም ብለዋል። ሚዲያዎችም የውይይት ባሕል እንዲዳብር ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት። ግጭት እና ጦርነት ለማንም እንደማይጠቅምም አስገንዝበዋል።
“ለግጭት ያበቃን አለመወያየት ነው” ያሉት ምሁሩ ሚዲያዎች በተቃራኒ ወገኖች ያሉ ኃይሎች እንዲወያዩ መጋበዝ አለባቸው፤ እምቢ ያለውን ደግሞ ማጋለጥ አለባቸው፤ ይህ ሲኾን ይጋለጣል ሕዝብ ይታዘባል ነው ያሉት። ለውይይት አለመሰልቸት ይገባል፤ ከጦርነት አዙሪት የውይይት አዙሪት የተመረጠው እና የተሻለው ነው፤ ውይይት ደግሞ ደም ከመፋሰስ እና ከሞት የተሻለው ነው ብለዋል። ሚዲያዎች የፖለቲካ ቀውስን ማረጋጋት እንደሚገባቸውም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!