
ደባርቅ: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ ላለፉት ሦሥት አሥርት ዓመታት ሀገራዊ አንድነት እና ብሔራዊ መግባባት እንዲጎለብት ኀላፊነቱን የተወጣ ተቋም ነው ሲሉ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አሚኮ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን ዕድገት ታሪክ ውስጥ ስማቸው ከሚጠቀሱ የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኅን አውታሮች መካከል አንዱ ነው። የተቋሙን 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ ሃሳባቸውን ያጋሩን የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክንዴ ተፈራ ተቋሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ሀገራዊ እና ክልላዊ ኀላፊነቱን በላቀ ብቃት ሲወጣ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ክልላዊ እና ሀገራዊ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በማገዝ ከፍተኛ ሚና እንደነበረውም አብራርተዋል። አሚኮ ከዘመን ጋር ተዋህዶ በሂደት ራሱን ያበቃ እና የራሱን ቀለም የፈጠረ ተቋም ነውም ብለዋል። ማኅበራዊ፣ ታሪካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን የተለያዩ መረጃዎች በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ የማኅበረሰቡን የመረጃ ተደራሽነት መብት ያከበረ ተቋም እንደኾነም ጠቁመዋል።
ተቋሙ አሁን ከደረሰበት የልህቀት ማዕከልነት ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፉን የገለጹት አቶ ክንዴ በቀጣይም የአማራ ሕዝብ ከተቋሙ ብዙ ይጠብቃል ነው ያሉት።
አሚኮ ያነጋገራቸው የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው አሚኮ በተለያዩ አማራጭ የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች ተደራሽነቱን እያሳደገ የመጣ ተቋም ነው ብለዋል። አሚኮ ልዩነትን አቻችሎ፣ አንድነትን አጉልቶ እና ማንነትን አክብሮ ሀገራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ ተቋም ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። ተቋሙ በዘገባ ሥራዎቹ አዝናኝ እና አስተማሪ ጥንቅሮችን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ እያደረገ የሚገኝ ተቋም መኾኑንም ጠቅሰዋል። በቀጣይም ተቋሙ ሀገራዊ እና አህጉራዊ ተደራሽነቱን በማሳደግ የስኬት ጉዞውን ሊያስቀጥል እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን