
አዲስ አበባ: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የመንገድ ዘርፍ ሁለተኛ ጉባኤ “ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ” የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ድኤታ የትምጌታ አስራት “የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ መንገድ የማይተካ ሚና እንዳለው” አንስተዋል። መንግሥት የዜጎችን ማኅበራዊ ትሥሥር ለማጠናከር እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን እየገነባ መኾኑን ገልጸዋል። እንደ ሀገር ባለፈው ዓመት 171 ሺህ ኪሎ ሜትር የነበረው የመንገድ አውታር መጠን አሁን ላይ ከ180 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መድረሱን ነው ሚኒስትር ድኤታው የተናገሩት። ይህ የመንገድ ግንባታ በትሪሊዮን የሚገመት ሃብት ኢንቨስት የተደረገበት መኾኑን ጠቁመዋል። ባለድርሻ አካላት መንገዶችን መጠበቅ እና መንከባከብ እንዳለባቸውም በአጽንኦት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ትሁን እንጅ አሁን ላይ ያለው የመንገድ አውታር መጠን በቂ አይደለም ብለዋል። ዛሬም ድረስ በመንገድ መሠረተ ልማት እጥረት ዜጎች ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተዳረጉ እንደኾነ ነው የገለጹት። በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሂደት የግንባታ ቦታዎች ከሦስተኛ ወገን አለመጽዳት፣ የካሳ ክፍያ መዘግየት፣ የግንባታ ግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ የሥራ ተቋራጮች አቅም ውስንነት፣ የዋጋ መናር እና የጸጥታ ችግር ለፕሮጀክቶቹ መጓተት እና ለሕዝብ ቅሬታ መጨመር ምክንያት መኾናቸውንም አንስተዋል።
የዜጎችን የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት የመንገድ ሴክተሩ የመፈጸም እና የማሥፈጸም አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት ነው የተናገሩት። የምንገነባው መንገድ ብቻ ሳይኾን ሀገርም ነውና መንገዶችን ስንገነባ በጥራት፣ በብቃት እና በታማኝነት ሊኾን ይገባል ብለዋል ሚኒስትር ድኤታው።
ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!