
አዲስ አበባ: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከበዓላት እና ከመንግሥት የደሞዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መኾኑን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ገልጿል።
ጉዳዩን አስመልክተው የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኀላፊ ጃንጥራር አባይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ጋዜጣዊ መግለጫው ትኩረት ያደረገው የዋጋ ንረት እና አቅርቦትን በተመለከተ ነው። በመዲናዋ አዲስ አበባ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር እና የገበያ መረጋጋትን ለማስፈን ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት። ገበያ እንዲረጋጋ፣ ሕገወጥ ንግድ ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገባ ከተማ አሥተዳደሩ የገበያ ማረጋጋት፣ የሕገወጥ ንግድ ቁጥጥር እና የኢትዮጵያ አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ግብረ ኀይል አቋቁሞ እየሠራ መኾኑንም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት በርካታ ሥራ ተሠርቷልም ነው ያሉት። በቂ የገበያ ቦታ ለማዘጋጀት በከተማዋ መውጫ እና መግቢያ በሮች ሰባት የገበያ ማዕከላት እየተገነቡ እንደኾነም አስረድተዋል። እየተገነቡ ካሉ የገበያ ማዕከላት ውስጥ አምስቱ ግንባታቸው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡ በአምስት ሁለገብ የግብርና ማዕከላት ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሰብል፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ይዘው ግብይት በመፈፀም አምራች እና ሽማችን በማገናኘት የሦሥተኛ ወገን ተፅዕኖን መቀነስ መቻሉንም ገልጸዋል። በ2017 ዓ.ም በገበያ ማዕከላት 371ሺህ 747 ኩንታል ሰብል እና 1ሚሊዮን 583ሺህ 419 ኩንታል የአትክልት እና ፍራፍሬ፣ 445ሺህ በላይ የዳልጋ ከብት እና 2ሚሊዮን 172ሺህ በላይ በግና ፍየል ለገበያ መቅረቡንም ተናግረዋል፡፡
የገበያ ማዕከላት ገበያን በማረጋጋት፣ አምራች እና ሸማች በማገናኘት ብሎም ከገበያ ዋጋ ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ዝቅተኛውን ማኅበረሰብ ለመደገፍ ጥረት ተደርጓልም ብለዋል፡፡ በተሠራው ሥራም በሰብል ምርት ከፍተኛ የኾነ የገበያ ማረጋጋት እና የዋጋ ቅናሽ የታየ ሲኾን በአትክልት እና ፍራፍሬ መጠነኛ ቅናሽ እንዲኖር መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡ ከበዓላት ጋር በተያያዘ የምርት አጥረቶች እንዳይኖሩ እየተሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ከተፈቀደው የደመወዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዳይከስትም በጥብቅ ቁጥጥር እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል በጋዜጣዊ መግለጫቸው፡፡ የዋጋ ንረት እና አቅርቦትን ለመከታተል ከላይ እስከ ታች ድረስ ግብ ኀይል ተዋቅሮ እየተሠራም ይገኛል ነው ያሉት፡፡ የከተማዋ ሕዝብ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከአሥተዳደሩ ጋር ተቀራርቦ እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሃመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን