
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከአራት ዓመታት በፊት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያረጀ ወይም የተበላሸ የላፕቶፕ ባትሪ መልሶ አገልግሎት ላይ እንዲውል የሚያደረግ ቴክኖሎጂ መሥራቱን ዘግበን ነበር፡፡ አብመድም ይህ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መለስ ብሎ ቃኝቷል፡፡
ዶክተር ሙሴ ይባዜ ቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት የላፕቶፕ ባትሪ በቴክኖሎጂው እንዲሞላ ከተደረገላቸው በኋላ ለሁለት ዓመት ከአምስት ወር ገደማ ያለችግር ተገልግለውበታል፡፡ መጀመሪያ እንደተሞላ አካባቢም ከአራት እስከ አምስት ሰዓታት መጠቀም ያስችላቸው እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
ለረጅም ሰዓት ቀጥታ ኃይል እንዲያገኝ ሰክቶ ማቆየትና የመሳሰሉት የአጠቃቀም ችግሮች ስለሚስተዋሉ እንጂ ቴክኖሎጂው ባትሪን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል በኩል መልካም ፈጠራ መሆኑን እንደተገነዘቡም ተናግረዋል፡፡
ጎንደር ከተማ አስተዳደር ውስጥ ሁለት ቦታ በሰለጠኑ ወጣቶች ባትሪ መሙላት በሚያስችለው ቴክኖሎጂ በንግድ ሥራ ላይ እንደተሠማሩበት የነገሩን ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ውለታው መኩሪያ (ዶክተር) ናቸው፡፡ ሥራው በደባርቅና በባሕር ዳር በወጣቶች እንደቀጠለ መረጃው እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂው ለመምህራንና ለተማሪዎች ነፃ አገልገሎት መስጠቱ እንዳልተቋረጠም አስታውቀዋል፡፡
ነገር ግን ይህ ቴክኖሎጂ በሚጠበቀው መልኩ እንዳልሰፋና እንዳላደገ ለመረዳት ችለናል፡፡ ወደፊት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ወደ “ቢዝነስ ኢንኩቤሽን ማዕከል” በማዛወር ለማሳደግ መታሰቡንም ዶክተር ውለታው አመላክተዋል፡፡ ሆኖም በዩኒቨርሲቲው ከተሠሩት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ውስጥ ከግቢው ወጥቶ ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ወጣቶች በየጊዜው ከጎናቸው ባለመለየት መደገፍ እንደሚጠበቅም ዶክተር ውለታው ገልጸዋል፡፡
በዚህ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ትልቁ አስተዋፅኦ ያበረከቱት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪውና የበርካታ ፈጠራዎች ባለቤቱ አቡሃይ ውብሸት ‘‘ያለው ጊዜና ለፕሮጀክቱ የተለቀቀው ገንዘብ ተመጣጣኝ አይደለም’’ ብለዋል፤ በዚህም ሥራው የበለጠ እንዲያድግና እንዲሰፋ አለመደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ተመራማሪ አቡሃይ እንዳሉት ያረጀ ወይም የተበላሸ ባትሪ መሙላት ብቻ ሳይሆን ባትሪውን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እስከ ማምረት ማደግ እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶክተር) ባትሪውን ማምረት እንደሚቻል ሐሳቡ ተገልፆላቸው በሐሳቡ መስማማታቸውንና ቅርጹን ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር እንዲወሰን ለማድረግ በሂደት ላይ እያለ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱንም ተመራማሪው አስታውሰዋል፡፡
አብመድ በቴክኖሎጂው በመጠቀም የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን ማግኘት ባይችልም ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ባትሪው ዳግም ወደ አገልግሎት እንዲመለስ የሚያደርገውን ኬሚካል ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ መውሰድ ማቋረጣቸውን ከተመራማሪው መረዳት ችሏል፡፡
ወጣቶቹ እንደየባትሪ ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ከአዲሱ ባትሪ በግማሽ ዋጋ ቀንሰው የደከመ ባትሪን እንደሚሞሉ ከተመራማሪው አብመድ አረጋግጧል፡፡ ለአብነት የ‘ሳምሰንግ’ እና “አፕል” ላፕቶፕ ኮምፒውተር ገበያ ላይ አዲሱ ባትሪያቸው 3 ሺህና ከ3 ሺህ ብር በላይ ሲሆኑ የሰለጠኑት ወጣቶች በ1 ሺህ 5 መቶ ብር እንደሚሠሩ ማወቅ ተችሏል፡፡
ባትሪውን ወደ ማምረቱ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚያስፈልግና ለሙያው የቀረቡ ምሁራን (ተመራማሪዎች) ጋር በመሆን በድጋፍ መሠራት እንዳለበት አቶ አቡሃይ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
ፎቶ፦ ካይንድ ፒ ኤን ጂ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡