
ደሴ: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮች ላይ ተመካክሮ ለሃሳብ ልዩነቶች መፍትሄ በማቅረብ መግባባት ላይ እንዲደረስ ጥረት የሚያደርግ ተቋም ነው።
ኮሚሽኑ “የወጣቶች ሚና እና ተሳትፎ ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት በደሴ ከተማ ለወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው። በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ከተለያዩ አከባቢዎች የተውጣጡ ተሳታፊ ወጣቶች የምክክር ኮሚሽኑ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ለማድግ ጥሩ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ወጣቱ ግንባር ቀደም ተሳታፊ መኾን ይገባዋልም ነው ያሉት። መመካከር ሰዎኛ እና የሥልጡን ሕዝቦች መገለጫ ነውም ብለዋል። ወጣቱ ዘርፈ ብዙ እና በሀገሪቱ ሰፊ ድርሻ ያለው እንደመኾኑ በሀገራዊ ምክክሩ እንዲካፈል መደረጉ የምክክር ኮሚሽኑ አካታች እንዲኾን ያደርገዋል ነው ያሉት።
ወጣቶች በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ንቁ ተሳታፊ በመኾን ለዘመናት ያልተመለሱ የወጣቱ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ብሎም ሀገራቸው አንድነቷን ጠብቃ ዘላቂ ሰላም እንድታገኝ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል። ወጣቶች ግንዛቤ እንዲያገኙ እና እምቅ አቅማቸውን ለሰላም እንዲያውሉ ለማድረግ እንደሚሠሩም ነው ተሳታፊዎች የተናገሩት። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በኢትዮጵያ በተከናወኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዩች ዙሪያ ወጣቶች የነበራቸው አሉታዊ እና አዎንታዊ ሚና የጎላ መኾኑንም አመላክተዋል።
በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የወጣቶች ሚና እንዲጎለብት እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ታምኖበት እየተሠራ ነውም ብለዋል። በኢትዮጵያ በሚነሱ ግጭቶች ወጣቱ ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ መኾኑን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ ወጣቱ በምክክር ሂደቱ ተጠቃሚ እንደሚኾንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል የሚወሰነው በወጣቶች መኾኑንም ጠቅሰዋል። “ወጣቱ ትውልድ ምክክር አዋጭ የችግር መፍቻ መንገድ መኾኑን አውቆ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል” ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ።
ዘጋቢ:-መስዑድ ጀማል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን