
ባሕር ዳር: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “በዲጂታል ዕውቀት እና ክህሎት የታነፀ ትውልድ ለአሻጋሪ እና ዘላቂ ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት የዲጂታል አማራ ኢኒሼቲቭ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የውይይቱ ተሳታፊዎች ዲጂታልን ዕውን ማድረግ ግዴታ መኾኑን ገልጸዋል። ዲጂታልን ዕውን ለማድረግ ደግሞ የዲጂታል መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ይጠበቃል ነው ያሉት። ዲጂታል አማራ ዕውን እንዲኾን እንደሚሠሩም ገልጸዋል። ተጀምሮ እንዳይቀር በትኩረት እና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ነገን ለሚያስብ ትውልድ ቴክኖሎጂ ግዴታ ነው ብለዋል።
ትውልድን በቴክኖሎጂ ማብቃት በውዴታ ብቻ የሚሠራ ሳይኾን ግዴታም ያለበት መኾኑን ተናግረዋል። ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ዕውቀት እና ገንዘብ እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት። ሥራ ፈጣሪ ትውልድ መፍጠር ከተፈለገ በቴክኖሎጂ እንዲካን ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ሀገር ተረካቢ ትውልድ ላይ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። ትውልዱ ሥራ ፈጣሪ እንዲኾን እንደሚሠራም አመላክተዋል። ትውልድን ለመገንባት በቅድሚያ መምህራን ላይ እንደሚሠራም ገልጸዋል። የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትን ለማሟላት የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል።
የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ድርጅት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ተከሰተብርሃን አድማሱ (ዶ.ር) የተጀመረውን ሥራ በቀላል መመልከት እንደማይገባ ተናግረዋል። የተጀመረውን በአግባቡ መጠቀም ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣም ነው የገለጹት። በአማራ ክልል በሚቀጥለው ዓመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በቴክኖሎጂ የበቁ ለማድረግ እንደሚሠራም ተናግረዋል። እያንዳንዱን ሥራዎች እና አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል። ሁሉም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የኢትዮጵያ አንደኛው የልማት ዘርፍ የቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ መኾኑን ገልጸዋል። ቴክኖሎጂ በራሱ ልማት ነው፤ ሌሎች ልማቶችን ለማሳለጥም ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል የአሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ የቴክኖሎጂ ልማትም ትኩረት እንደተሰጠው አመላክተዋል። ቴክኖሎጂን መተግበር ተጀምሮ እንደማይተው እና በዘላቂነት እንደሚሠራም አስታውቀዋል። ዲጂታላይዜሽን ዕውን እንዲኾን ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባም አመላክተዋል። መሪዎች ለዲጂታላይዜሽን ትኩረት እንዲሰጡም አሳስበዋል። ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ቴክኖሎጂን መጠቀም ግዴታ ነው ብለዋል። ዲጂታላይዜሽን ሂደት እንደኾነ እና ቀጣይነት እንዳለው አመላክተዋል። ዲጂታላይዜሽንን መጠቀም በሁሉም ዘርፎች እንደሚሠራበትም ገልጸዋል።
ዲጂታላይዜሽንን እውን ለማድረግ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል። መሪዎች ሥራው ውጤታማ እንዲኾን በትኩረት እንዲሠሩም ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን