
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጢስ ዓባይ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ በላይነህ አየለ (ዶ.ር) ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት፣ ለውጥና የማኀበረሰብ ሽግግር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመማር እድሉን ላላገኙ ተማሪዎች የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ክፍተቱን ለመሙላት ሚናቸው የላቀ መኾኑንም አንስተዋል። ጢስ ዓባይ ኮሌጅም ይህንን የተደራሽነት ክፍተት በመሙላት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደኾነ ተናግረዋል። ተመራቂዎች በኮሌጁ ተምረው ያገኙት ዕውቀት በቀጣይ ራሳቸውን ለማብቃት ለሚያደርጉት ምርምር እንደ መስፈንጠሪያ የሚያገለግል መኾኑን ነው የገለጹት።
“ተመራቂዎች ሁሌም አንብቡ፣ ተፈጥሮን መርምሩ፣ በዕውቀት ተመሩ፣ ለእውነት ቁሙ፣ ያገኛችሁት ዲፕሎማና ዲግሪ የሚያስከብራችሁ እንጂ የሚያስወቅሳችሁ መኾን የለበትም” ብለዋል። በትምህርት ተቋም ገብቶ መመረቅ በተወሰነ የትምህርት መሥክ ተምሮ ማለፍን የማረጋገጫ ሥርዓት እንጂ በሙያው ያለውን ዕውቀት ማጠናቀቅ እንዳልሆነ አመላክተዋል። ምንም ያህል ዕውቀት ቢኖረን ክህሎት ከሌለ ዋጋ የለውም ያሉት ዶክተር በላይነህ “የተመረቀባችሁበትን የምስክር ወረቀት የሚመጥን ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ሊኖራችሁ ይገባል” ነው ያሉት። ለዚህም ሁሌም ተማሪ መኾን ይጠበቅባችኋል ብለዋል። ከዘልማዳዊ አስተሳሰብ በመውጣት፣ ሁልጊዜ ቅጥርን ከመጠበቅ ይልቅ ሥራ ፈጣሪ መኾን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በቀጣይ ተመራቂዎች በሚሰለፉበት የሥራ መሥክ ተገልጋዮችን በቅንነት፣ በታማኝነት እና በሀቀኝነት እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጢስ ዓባይ ኮሌጅ ዲን ስለሽ ጎሹ ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ባለፈ ለባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢው የሥልጠና ማዕከል በመሆን እየሠራን መኾኑን ተናግረዋል። ተመራቂዎች በፊታችሁ ያለውን ረጅም ጉዞ ለመጨረስ አኹን አንድ እርምጃ ተጉዛችሁ ለስኬት በቅታችኋል ብለዋል፡፡ በኮሌጁ ተምረው የያዙት ዲግሪ የመጀመሪያ ምዕራፍ እንጂ የመጨረሻ እንዳልኾነም ነው የገለጹት። ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት የበለጠ በማጠናከር ለበለጠ ውጤት ጠንክረው መሥራት እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል።
ሥራ ወዳድ፣ ታታሪ፣ በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲኾኑ በኀላፊነት ሀገር ተረካቢ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በኮሌጁ በፕሮጀክት አሥተዳደር የማስተርስ ዲግሪ ተመራቂ የኾኑት ሙሉዓለም ባይሌ አኹን ላይ በባንክ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሰማርተው እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በተመረቁበት የሙያ መስክ ለሚሠሩበት ተቋም የተሻለ ሥራ ለመሥራት ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት። ሌላኛው በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ተመራቂና በኮሌጁ የዋንጫ ተሸላሚ አታለል ይግዛው ከመንግሥት ሥራ ከመጠበቅ ይልቅ በግሉ ሥራ ፈጥሮ ለመሥራት እንደሚመርጥ ተናግሯል። በቀጣይም ከሥራ ጎን ለጎን ትምህርቱን ለማሻሻል እንደሚቀጥል ገልጿል። ኮሌጁ ዛሬ ያስመረቃቸው ተመራቂዎች በቴክኒክና ሙያ፤ በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ 756 የሚኾኑ ተማሪዎች ናቸው። ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 234ቱ ደግሞ ሴቶች መኾናቸው ነው የተመላከተው።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን