የአሚኮ የቴክኖሎጅ ጉዞ-ሁለት

5
ባሕር ዳር: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአሁኑ አሚኮ እንዲወለድ የብዙ ዓመታት ውጣ ውረድ እና መስዋዕትነት ተከፍሎበታል፡፡
ጅማሮው ‘ከምንም’ ነው በማለት ይገልጹታል አብረውት ዛሬ ላይ የደረሱ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፡፡ ‘ከምንም’ ማለታቸው በወቅቱ የነበረውን ያልተሟላ የሥራ ከባቢ፣ የሚዲያ ቁሳቁስ አለመሟላት እና የቴክኖሎጂ አለመዘመንን ለመግለጽ እንጂ የሙያ ፍቅር፣ ሥነ ምግባር እና ዛሬን አሻግሮ ማየት የሚችል ቁርጠኝነት የነበራቸው ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ አሚኮ በ30 ዓመታት የቴክኖሎጂ ጉዞው ያለፈባቸው የቀረጻ እና ስርጭት ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኋላ ስንመለከት በሦስት አስርት ዓመታት የተደረገውን የቴክኖሎጂ ሽግግር በአግባቡ ማሳየት ያስችላል፡፡
የቀረጻ ሥራ እንዴት ተጀመረ ስንል ከጅማሮው ስያሜ አማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት እስከ አሁኑ አሚኮ አብሮ ዛሬ ላይ የደረሰው የቀረጻ፣ ቅንብር እና ግራፊክስ ዳይሬክተር የሺዋስ አጥናፉ ጋር አውርተናል፡፡ አቶ የሺዋስ የቀረጻ ቴክኖሎጂው ምን እንደሚመስል በምልሰት ሲያስቃኘን የሚዲያ ሥራ የዝግጅት ምዕራፍ ከተጀመረበት የክልሉ ማስታወቂያ ቢሮ ተነሳ፡፡ የቪ.ኤች. ኤስ ክር (ካሴት) የሚወስዱ ካሜራዎች ለቀረጻ ሥራ ‘ሀ’ የተባለባቸው ነበሩ፡፡ ቪ.ኤች.ኤስ (Video Home System) የጃፓኑ ጄ.ቪ.ሲ የኤሌክትሮኒክስ ማምረቻ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1976 ዓ.ም ያስተዋወቀው ቆየት ያለ ለቀረጻ አገልግሎት የሚውል ክር (ካሴት) ነው፡፡ ይህን ክር የሚጠቀሙ ካሜራዎች ናቸው ለዛሬ መሠረት የጣሉት፡፡
ይህ ካሜራ ለሚዲያ ሥራ ተብሎ የተዘጋጀ ሳይኾን ለቤት ውስጥ አገልግሎት ማለትም ለሠርግ፣ ለልደት እና መሰል ዝግጅቶች በሚል የሚመረት መኾኑን እና ከሁለት እስከ ሦስት ኪሎ ግራም የሚመዝን መኾኑን ነግረውናል፡፡ ቪ.ኤች.ኤስ ካሜራን ተከትሎ አድጎ የመጣው የቀረጻ ቴክኖሎጂ ሚኒዲቪ ክሮችን የሚወስዱ ናቸው፡፡ በመጠናቸው አነስ ያሉ፣ ቀላል እና ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የማያስቸግሩ ናቸው፡፡ የምስል ጥራታቸውም የተሻሉ ነበሩ፡፡ በአሚኮ የቀረጻ ሥራ ልዩ ታሪክ ያለው በ1982 የሶኒ ድርጅት ያስተዋወቀው ቤታ ካም ነው፡፡ አሚኮ ይጠቀምበት የነበረው ቤታ ካሜራ 10 ኪሎ ግራም እንደሚመዝን እና ክብደቱ በትከሻ ላይ አድርጎ ለመሥራት እንደሚመች አቶ የሺዋስ ገልጸውልናል፡፡
የቤታ ካሜራ ባትሪዎች ቶሎ ቶሎ ያልቁ ስለነበር ለዘገባ ሥራ ቅዝቃዜ ያለባቸው ደጋማ አካባቢዎች ሲኬድ ባትሪዎቹ በቅዝቃዜ ምክንያት ኃይል እንዳይጨርሱ ሙቀት ለመስጠት ሲባል ሹፌር፣ ካሜራ ባለሙያ፣ ረዳት ካሜራ ባለሙያ እና ሪፖርተር እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ባትሪ አቅፈው መተኛት ይጠበቅባቸው እንደ ነበር ነግረውናል፡፡ እንደ መጠኑ ታሪኩ የገዘፈው ቤታ ካም የያዘው ምስል ጥራት ምን ይመስል እንደ ነበር ለማየት የሚያስችል አነስ ያለ ቴሌቪዥን መሰል መመልከቻም ነበረው፡፡ ለሥራ ሲወጣ ይህ መሳሪያም አብሮ መውጣት ግድ ይለው ነበር ሲሉም አጫውተውናል፡፡
በቂ ብርሃን በማይኖርበት ቦታ በቤታ ካሜራ ቀረጻ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በኤሌክትሪክ ገመድ በማገናኘት የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ኾነው የሚያገለግሉ ተቀጣጥለው እንደ ዝናር በወገብ የሚታሠሩ የፓግ ላይት (PAG light) ባትሪዎች የነበራቸው ሚና ትልቅ ነበር፡፡ ተሳስረው አንድ ወጥ ኾነው በወገብ የሚታሠሩት የፓግ ላይት ባትሪዎች 16 ኪሎ ግራም ይመዝኑ ስለነበር የቤታ ካም ባለሙያ በአጠቃላይ 26 ኪሎግራም የሚመዝን የቀረጻ መሳሪያ ይዞ እንዲሠራ ግድ ይለው ነበር፡፡ ለዛም ነው በወቅቱ ረዳት ካሜራ ባለሙያ ይቀጠር የነበረው፡፡ ይህን ተሸክሞ ተራራ መውጣት መውረድ እና የእግር ጉዞ አድርጎ ተንቀሳቅሶ መሥራት ምን ያህል ከባድ እንደኾነ ለመገመት አይከብድም፡፡ ቤታ ካምን ተከትሎ ዲቪ ካም ሲመጣ የቴክኖሎጂ ለውጡም በመጠን እና በምስል ጥራት እየተሻለ መጣ ያሉን ዳይሬክተሩ የቀረጻ ቴክኖሎጂው በሽግግር ሂደት ውስጥ እያለፈ እንደነበር አስታወሱን፡፡
ዲቪካምን ያስተዋወቀውም ሶኒ ነበር፡፡ በዘመን ለውጥ አብሮ እያደገ የመጣውን የጥራት ማሻሻያ እያደረገ ነበር ለገበያም ሲያቀርበው የቆየው፡፡
እነዚህን የቀረጻ ቴክኖሎጂዎች በዘመናት ጅረት ውስጥ እየተጠቀመ አሚኮ ኤክ ዲቪንም መጠቀም ጀመረ፡፡ ይህ ካሜራ አሁንም ድረስ በአገልግሎት ላይ ያለ ነው፡፡ የጥራት ደረጃውም ጥሩ እንደኾነ አቶ የሺዋስ ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ከነበሩት የካሜራ ቴክኖሎጂዎች ሁሉ የላቀው እና አሁንም በአገልግሎት ላይ ያለው ደግሞ 4 ኬ የሚባል የምስል ጥራት ያለው ካሜራ ነው፡፡ 4 ኬ ማለት ባለ 4 ሺህ ፒክስል ምስል ማለት ነው፡፡ የአሚኮ የቴክኖሎጂ ጉዞ በቀረጻ መሳሪያ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ አሁን ትልቅ የሚባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የታጠቁትን የሥርጭት መገልገያዎችንም ታጥቋል፡፡
በአሚኮ የሚዲያ ኦፐሬሽን ምክትል ዳይሬክተር የኾኑት አስማማው ደሴ በስርጭት በኩል ስላለው ዝማኔ ሲያስረዱ አሚኮ የአየር ሰዓት ወስዶ ከመሥራት ተሻግሮ የራሱን ስቱዲዮ ገንብቶ እና አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ምናባዊ ስቱዲዮ (ቨርችዋል ስቱዲዮ) ይጠቀም እንደነበር ገልጸው አሁን ግን በቪዲዮ ዎል አውዳዊ የኋላ (ባክግራውንድ) የኢንፎግራፊክስ ምስሎችን መጠቀም የሚያስችል ስቱዲዮ ባለቤት ኾነናል ብለዋል፡፡ አክለውም “ለየአንድ አንዷ ፕሮግራም አንድ አንድ ካሴት እንጠቀም ነበር፡፡ አሁን በሰርቨር በተሳሰረ ሥርዓት ያለ ካሴት መሥራት ችለናል” ሲሉ የዝማኔ ደረጃውን ተናግረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ በአሚኮ ታሪክ ትልቅ የሚባለው ቴክኖሎጂ ደግሞ ኦቢ ቫን (አውት ዶር ብሮድካስቲንግ ተሸከርካሪ) በማለት የምንጠራው ተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ ነው፡፡ ቀጥታ ስርጭት ከየትም ቦታ ኾኖ ማስተላለፍ የሚቻልበት፣ ለኳስ ጨዋታ ስርጭት ምልሰት (ሪፕሌይ) ያለው እና ተቋሙን ወደ ላቀ ከፍታ የሚወስድ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአሚኮ የቴክኖሎጂ ጉዞ ወደ ሳይበር ዓለምም ገብቶ ብዙዎችን እየደረሰ እና ተጽዕኖ እየፈጠረም ይገኛል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበገንዳ ውኃ ከተማ የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር ተካሄደ።
Next articleተመራቂዎች ቅጥርን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ ሥራ ፈጣሪ መኾን ይገባቸዋል።