
ገንዳ ውኃ: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ሰንበት ትምህርት ቤት እና የመተማ ወረዳ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በጋር በመኾን አቅም ለሌላቸው ዜጎች ማዕድ የማጋራት መርሐ ግብር በገንዳ ውኃ ከተማ አካሂደዋል።
የማኅበረ ቅዱሳን ፀሐፊ እና አስተባባሪ አዛነው ታከለ የፍልሰታ በዓልን ምክንያት በማድረግ አቅም ለሌላቸው ዜጎች የማዕድ ማጋራት ተግባር እያከናወኑ መኾናቸውን ተናግረዋል። ማኅበሩም ዛሬ ከ400 በላይ አቅም የሌላቸውን ዜጎች ማዕድ እንዳጋሩ አቶ አዛነው ገልጸዋል። ይህም ከመንግሥት ሠራተኞች፣ ከባለሃብቶች፣ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ከማኅበረሰቡ መዋጮ በማሠባሠብ ማዕድ ማጋራት መቻላቸውን ነው የጠቆሙት።
ቅን ልቦች ባዋጡት መዋጮ ሥራውን ማከናወናቸውን ተናግረው በቀጣይም ከዚህ በበለጠ ለመሥራት የሁሉንም ማኅበረሰብ ድጋፍ ማኅበሩ እንደሚሻ አመላክተዋል። በጎነት ለራስ መኾኑን ፀሐፊው ጠቁመው ሁሉም አካላት ላደረገው ትብብር ምሥጋና አቅርበዋል። በቀጣይም የማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዳይለያቸው አሳስበዋል። ሌላኛው አስተባባሪ አቶ መኮንን መንገሻ በማኅበሩ ለረጅም ዓመታት እንዳገለገሉ ገልጸው ይህን የበጎ ተግባር ሥራ በመሥራታቸው ሁሌም ደስተኛ መኾናቸውን ነግረውናል።
አቅመ ደካሞችን በማግደፍ አብሮነትን እና መተሳሰብን በማጠናከር ለላይኛው ዓለም ተስፋ የምንሰንቅበት መርሐ ግብር ነው ብለዋል።
ይህን መልካም ተግባር ለማስቀጠል ማኅበረሰቡ እንዲሳተፍም አሳስበዋል። ማዕድ ከተጋሩት ተሳታዎች መካከል አቶ ሞገስ መንግሥቱ እና ወይዘሮ እናኑ ረታ ማዕድ በመጋራታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸው ለተደረገላቸው መልካም ተግባርም ምሥጋና አቅርበዋል። አቅም የሌላቸው ዜጎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን