
ባሕር ዳር: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ውግንናው ለሕዝብ ስለኾነ በመሰዋዕትነት ውስጥ ኹሉ እያለፈ ትውልድ ያሰቀጠለ እና ሀገር ያጸና የሚዲያ ተቋም መኾኑ ተገልጿል።
የቀድሞው የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት የአሁኑ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ታኅሣሥ 07/1987 ዓ.ም በበኩር ጋዜጣ ኀብረተሰብን የማስተማር፣ የማዝናናት እና የማሳወቅ ተልዕኮን አንግቦ ተጀምሯል። በሂደትም በቴሌቪዥን፣ በመደበኛው ሬዲዮ፣ በኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96.9፣ በብሔረሰብ ጋዜጦች እና በዲጂታል ሚዲያ አማካኝነት አድማሱን በማስፋት እነሆ 30 ዓመታትን ተሻግሯል። አሚኮ በርካታ የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ዜጋ ተኮር ሥራዎችን አከናውኗል። እያከናወነም ይገኛል። በተለይም ለሀገር ልዑላዊነት መከበር፣ ለሰላም እና ጸጥታ መስፈን አሚኮ የነበረው አበርክቶ ከፍተኛ ነው።
በ1990ዎቹ የኤርትራ መንግሥት በእብሪት ተነሳስቶ ድንበር ተሻግሮ በመምጣት በሕዝብ ላይ ግፍ መፈጸሙ ይታወሳል። በዚህ ወቅት መላው ኢትዮጵያውያን በአጥንት እና ደሙ የሀገሩን ልዐላዊነት እንዲያስከብር አሚኮ ሀገራዊ ድርሻውን አበርክቷል። የጋዜጠኞችን ቡድን ግንባር ድረስ በማዝመትም ሚዛናዊ መረጃ ለሕዝብ፣ ለመንግሥት እና ለዓለም ማኀበረሰብ በማድረስ የውዴታ ግዴታውን ተወጥቷል። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት አሚኮ ከደጀንነት እስከ ግንባር በመዝመት ተአማኒ መረጃ ለሀገሬው እና ለዓለም ማኀበረሰብ በማድረስ ውግንናው ሕዝብ መኾኑን አስመስክሯል። በሀገሪቱ በየትኛውም አቅጣጫ የደረሰን ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በመዘገብ በሕዝብ ላይ ሊደርስ የሚችልን ተጨማሪ ጉዳት እንዲቀንስ፣ የሰብዓዊ እርዳታ በፍጥነት እንዲደርሰ የማሳወቅ እና የማንቃት ሥራ በትጋት አከናውኗል።
“ነገርን ከሥሩ፤ ውኃን ከጥሩ” ነውና ብሂሉ ከሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም ወንጀልን ቀድሞ ከመከላከል አኳያ የነበረውን የአበርክቶ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ “የእንኳን አደረሳችሁ” መልዕክታቸውን አስቀድመው አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት ለክልሉ ብቻ ሳይኾን ለመላው የሀገሪቱ ሕዝብ ‘ዕውነተኛ ድምጽ’ ኾኖ የዘለቀ ሚዲያ ነው ሲሉ ገልጸውታል። ኢትዮጵያ በየጊዜው በገጠማት የሰላም እጦት ወቅት አሚኮ ከሚዛን ሳይወርድ እውነተኛ እና ትክክለኛ መረጃን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ምክትል ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። አሚኮ ምቹ ባልኾኑ ቦታዎች እና በጦርነት ወቅት ሁሉ እያለፈ ለሕዝብ ሰላም የነበረው አበርክቶ በታሪክ መዝገብ ውስጥ በደማቁ ተጽፎ ሊቀመጥ የሚችል ትውልድ አሻጋሪ ግዴታውን ተወጥቷል ነው ያሉት።
በቅርቡ ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ችግር ምክንያት አብዛኞቹ ሚዲያዎች ከሚዛን ሲወርዱ፣ ከሚጠበቅባቸው ኀላፊነት ዝቅ ሲሉ አሚኮ ግን ለሕዝብ ሰላም መስፈን መስዋዕትነት እየከፈለ ዕውነተኛ መረጃን ለኀብረተሰብ ተደራሽ አድርጓል። በዚህም አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ሠርቷል። የተገኘውን ሰላምም ለማጽናት አሚኮ የነበረው እና አሁንም ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ነው ብለዋል። በየአካባቢው ለሰላም የተደረጉ መድረኮችን በማኀበረሰቡ ውስጥ ኾኖ ኀብረተሰቡ የሚያነሳቸው ሐሳቦች በትኩሱ እና ሳይሸራረፉ ለሕዝብ ማድረሱን ነው አቶ በሪሁን የተናገሩት። “እንደ ከልል የገጠመው ችግር ምክንያቱ ምን ይኾን? መፍትሔውስ ምንድን ነው? ” በሚል የአማራ ክልል ሕዝብ ከቀበሌ እስከ ክልል ቢሮዎች ድረስ ውይይቶች ሲደረጉ ከሕዝብ የሚፈልቁትን ሐሳቦች መልሶ ለሕዝብ በማድረስ ረገድ የአሚኮ ሚና ከፍተኛ ነበር ነው ያሉት አቶ በሪሁን።
አሚኮ ውግንናውን ለሕገ መንግሥቱ እና ለሕዝብ በማድረግ እስካሁን የሄደበት ርቀት ለሌሎች ሚዲያዎችም አርዓያነቱ ከፍተኛ መኾኑን ምክትል ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር መሳይ ወርቁ በበኩላቸው አሚኮ ወንጀልን በመከላከል እና የጥንቃቄ መልዕክቶችን ለሕዝብ በማድረስ ረገድ የነበረው ሚና ጉልህ እንደነበር ገልጸዋል። የትራፊክ አደጋ እንዳይደርስ፣ ከደረሰ በኋላም ከአንዱ ስህተት ሌላው እንዲማር እና ቀጣይ አደጋ በእርሱ ላይ እንዳይደርስ የአሚኮ አበርክቶ ከቃል በላይ ነው ብለዋል።
የየትኛውም ሃይማኖት በዓል ሲከበር አሚኮ ደስታውን በጋራ በመደሰት፣ በደስታው መሐል ችግር እንዳይፈጠር የጥንቃቄ መልዕክት ተደራሽ በማድረግ አሚኮ የሕዝብ አጋርነቱን አስመስክሯል ነው ያሉት። ክልሉ በጸጥታ ችግር በነበረበት ወቅት ኀብረተሰቡ ወንጀልን በመጠየፍ በጋራ እንዲከላከል የሚያስችሉ መልዕክቶች በተደጋጋሚ ተሠርተዋል። እነዚህ መልዕክቶችም በእያንዳንዱ ማኀበረሰብ አዕምሮ ሰርጸው አዎንታዊ ውጤት አስመዝግበዋል ነው ያሉት። በየትኛውም አካባቢዎች ችግሮች ሲከሰቱ በሰላም ፣ በውይይት እና በምክክር እንዲፈቱ የሚደረጉ ጥረቶችን አሚኮ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮቹ በቀጥታ መረጃ በማድረስ ለሰላም መስፈን የነበረው አስተዋጽኦ ላቅ ያለ እንደነበር ኮማንደር መሳይ ተናግረዋል።
የክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ ዋና መምሪያ በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ ከአሚኮ ጋር እጅ እና ጓንት ኾኖ እንደሚሠራም አጋርነቱን ገልጸዋል።
አሚኮ ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ አራት ጋዜጦች፣ ሰባት ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ሁሉንም አማራጮች በያዘ የዲጂታል ሚዲያ ለኀብረተሰብ ለውጥ የሚተጋ የሕዝብ ሚዲያ ነው። የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች እንግሊዝኛ እና አረብኛን ጨምሮ ከሀገር ውስጥ ባሻገር ተደራሽ የኾነ ግዙፍ የሚዲያ ተቋም ነው።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን