ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ሩሲያ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አሳወቀች፡፡

254

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሕዳሴ ግድቡን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለችው መሆኑን ሩሲያ አስታውቃለች፡፡

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ዛሬ ሰኔ1 ቀን 2012 ዓም በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጄኒይ ተረክህንን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊና በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳለቸው ያነሱት አቶ ገዱ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። ሩሲያ ከአራት ቀናት በፊት ግንቦት 27 ቀን 2012 ዓ.ም ከኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቷ በኩል የሰጠችው መግለጫ አገሪቱ ለዓለም አቀፍ መርህ መከበር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን በማንሳትም አመስግነዋል፡፡

ሩሲያ ከግድቡ ጋር በተያያዘ እ.አ.አ ሰኔ 4 ቀን 2020 በሰጠችው መግለጫ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለችው መሆኑን መግለጧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በሦስቱ አገራት መካከል የሚደረጉ ውይይቶች የሁሉንም የተፋሰሱ አገራት የጸጥታና በውኃው በመጠቀም የመልማት መብት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መሆን አለበት የሚል እምነት እንዳላት መግለጿም ይታወቃል። ሦስቱ አገሮች ልዩነታቸውን እ.አ.አ በ2015 በደረሱት የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በውይይት እንዲፈቱ ሩሲያ ማሳሰቧ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጄኒይ ተረክህን በበኩላቸው ሩሲየ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ዋጋና ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ ሩሲያ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

Previous articleከአማራ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት አምስት ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ማገገማቸውን ጤና ቢሮው ገለጸ።
Next articleየላፕቶፕ ባትሪ መልሶ አገልግሎት ላይ እንዲውል የሚያደረገው ፈጠራ ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ አልተሸጋገረም፡፡