በባሕር ዳር ከተማ የንግድ ሥርዓቱን በሚያወኩት አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው።

8
ባሕር ዳር: ነሐሴ 17/12/17 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ሠራተኞችን የደመወዝ ጭማሪ መሠረት በማድረግ በንግዱ ዘርፍ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል።
መንግሥት ለመንግሥት ሠራተኞች ከመስከረም 2018 ዓ.ም የሚጀምር የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉ ይታወሳል። የአማራ ክልል ንግድ እና ገቢያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ መንግሥት ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ የመንግሥት ሠራተኞች ለማኅበረሰቡ የተቀላጠፈ፣ ፍትሐዊ እና ውጤታማ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል። መንግሥት የደመወዝ ጭማሪውን ይፋ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከፍትሕ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የንግድ እንቅስቃሴው ጤናማ ኾኖ እንዲቀጥል የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በተደረገው የቁጥጥር ሥራ አብዛኛው የንግዱ ማኅበረሰብ ጭማሪውን በአዎንታ ወስዶ ሕጋዊ መስመርን ተከትሎ እየሠራ ቢኾንም ጭማሪውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በምርቶች፣ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ምርት ከዝነው እና በአንዳንድ ምርቶች ላይ ዋጋ ጨምረው የተገኙ ነጋዴዎችን ምርት በሕጉ መሰረት በመውረስ ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ማከፋፈል መቻሉንም ነው የገለጹት። ምርቱን ከመውረስ ባለፈም የንግድ ፈቃዱን መሠረዝ ብሎም በሕግ ጭምር ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። እርምጃ ከመውሰድ ጎን ለጎን ለንግዱ ተዋንያን የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
አጠቃላይ ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ 2 በመቶ እንኳን ለማይሞላ የኅብረተሰብ ክፍል የደመወዝ ጭማሪ ተደረገ ተብሎ በሸቀጦች ላይ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ መላውን የሀገሪቱ ሕዝብ ጭምር ለከፋ ኑሮ እንዲጋለጥ ማድረግ ወንጀል እና ኢሞራላዊ መኾኑንም ገልጸዋል። የሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ ከምርት ዋጋ ጋር የሚያገናኘው ምክንያታዊ ነገር እንደሌለውም አንስተዋል። የንግዱ ማኅበረሰብ በምርቶች ላይ ዋጋ ጨምሮ መሸጥ ተቀባይነት የሌለው መኾኑን ተረድቶ በፍትሐዊነት እንዲሸጥ ጠይቀዋል። ሸማቹም ቢኾን ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ሲያጋጥሙት ተሻምቶ ከመግዛት ይልቅ በአቅራቢያው ለሚገኘው የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ እና ለፍትሕ ተቋማት ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። በየደረጃው የሚገኘው የመንግሥት መዋቅርም በተናበበ መንገድ በሕግ ወጥ ተግባር በተሳተፉ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል። ቢሮው በቀጣይም እርምጃውን አጠናክሮ የሚቀጥል ይኾናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየትምህርት መቋረጥ ትውልድን ለሥነ ምግባር ጉድለት ይዳርጋል።
Next articleየዲጂታል አማራ ኢኒሼቲቭ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።