
ባሕር ዳር: ነሐሴ 17/12/17 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት ባሕል እና እሴትን ለመጠበቅ እና ለማኅበረሰብ እድገት መሠረታዊ ነገር ነው፡፡
በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ ተቋርጦባቸውም ቆይቷል፡፡ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎች እንዲማሩ ሁሉም የድርሻውን ቢያበረክት ውጤቱ መልካም ይኾናል። ከዚህ አንጻር የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡
የአማራ ክልል የሽምግልና መማክርት ጉባኤ ሰብሳቢ መሪጌታ ብሩህ ዘላለም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ትምህርት እንዲጀመር ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ሁሉም የሀገር ሽማግሌዎች ቢቻል ሰላምን ለማምጣት ካልኾነ ደግሞ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ትምህርት እንዲሰጥ መሥራት አለባት ነው ያሉት፡፡ ምንም ቢኾን ትምህርት መቋረጥ የለበትም ብለዋል። ማንኛውም አካል ትውልድ እንዲማር ትምህርትን መፍቀድ አለበት፤ ለሁለት ዓመታት ትምህርት በመቅረቱ ያልተማረ ትውልድ እያስቀጠልን ስለኾነ ትምህርት መጀመር አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ሰብሳቢው በሚኖሩበት አካባቢ በገጠሩ ክፍል ትምህርት በመዘጋቱ ያለዕድሜያቸው ወደ ትዳር የገቡ ሴቶች በርካታ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ሴቶች ቀጣይ ትምህርት ቢጀመር እንኳን ልጅ በመውለዳቸው ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚቸገሩት ቁጥራቸው ብዙ ነው ብለዋል፡፡
“የትምህርት መቋረጥ ሥራ አጥነትን ያባብሳል፤ ትውልድንም ለሥነ ምግባር ጉድለት ይዳርጋል” ነው ያሉት፡፡ የመማክርት ጉባኤው በዞኖች ያሉ አባል የሀገር ሽማግሌዎችን በመጠቀም ትምህርት እንዲቀጥል እንሠራለን ነው ያሉት፡፡ ማኅበረሰባችን “ካልተማሩ አያውቁ ካላወቁ አይጸድቁ” የሚለውን ብሂል መሠረት በማድረግ የሰውን ልጅ ሰው የሚያሰኘው ዕውቀቱ እና ግንዛቤው መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል። ማኅበረሰቡ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በራሱ አቅም ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ልጆቹ እንዲማሩ ማድረግ አለበት ነው ያሉት፡፡
የመማክርት ጉባኤው ምክትል ሰብሳቢ ይመር ሰይድ ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ እና የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን እንዲከፈቱ ሁሉም የሀገር ሽማግሌዎች በየአካባቢያችን ከገጠር እስከ ከተማ መሥራት አለብን ብለዋል። ትምህርት እንዲዘጋ ያደረጉ አካላት የማኅበረሰቡ ክፍሎች በመኾናቸው ከቤተሰቦቻቸው እና ከእነሱም ጋር በመነጋገር ትምህርት መጀመር አለበት ነው ያሉት። ትምህርት በመቅረቱ ክልሉ በዕውቀት ወደ ኋላ እየቀረ እና እየተጎዳ ነው ብለዋል። ከረፈደም ቢኾን የመንግሥት አካል፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ኅብረተሰቡ እና ሁሉም በመረባረብ መመካከር እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ልጆቻችን እንዲማሩ መሥራት አለብን ብለዋል።
ሌላው ሃሳብ የሰጡን የሃገር ሽማግሌ የመማክርት ጉባኤው አባል አለቃ ጥላዬ አየነው በተለይም በገጠሩ የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ሰላም ወደኾነው ከተማ በመሄድ የተማሩ አሉ፤ ይህ ደግሞ ወላጆችን ለተጨማሪ ወጭ እንደዳረጋቸው አንስተዋል። አቅም ያልፈቀደለት ደግሞ ትምህርት አቋርጦ መቆየቱን ነው የገለጹት። ይህንን በመገንዘብ ማንኛውም አካል ልጆች እንዲማሩ፣ የወላጆች ድካም እንዲቀንስ እና ሀገር እና ሕዝብ በዕውቀት እንዲመራ መፍቀድ አለበት ሲሉ መክረዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!