
ደሴ፡ ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የሚኖሩት አቶ ሰይድ ያሲን እና ወጣት ኑሩ አያሌው በዶሮ እና በከብት እርባታ ላይ ተሰማርተው ትርፋማ እየኾኑ ነው።
አቶ ሰይድ ያሲን የዶሮ እርባታ ሥራቸውን የጀመሩት በ30 ዶሮዎች ነው። አሁን ግን ከ1 ሺህ በላይ ዶሮዎችን በማርባት በየቀኑ ከ700 በላይ እንቁላል እየሠበሠቡ ነው። አቶ ሰይድ እንደሚሉት የገበያ ትስስር ባለመኖሩ ምክንያት ነጋዴዎች በሚያወጡት የዋጋ ተመን እንቁላል ለመሸጥ ይገደዳሉ። ወጣት ኑሩ አያሌው ደግሞ በአምስት ዓመታት ውስጥ የከብት እርባታ ሥራውን ከሁለት ላሞች ጀምሮ አሁን ላይ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ከብቶች ባለቤት መኾን ችሏል። በከተማ አሥተዳደሩ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ላይ ወተት በማቅረብም የገበያ ትስስር እንደተፈጠረለት ገልጿል።
አቶ ሰይድ ያሲንም ኾኑ ወጣት ኑሩ ምርታቸውን ይበልጥ በማሳደግ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ ለማቅረብ እና ሥራቸውን ለማስፋፋት የቦታ ማመቻቸት እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት የ010 ቀበሌ የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ባለሙያ ጀማል አሰፋ በእንስሳት እርባታ የተሰማሩ ነዋሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ሙያዊ ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል። የእንስሳት ወረርሽኝን ለመከላከል በየሦሥት ወሩ ክትባት እየተሰጠ እና የምርታማነትን መጠን ለመጨመርም የተሻለ መኖ እንዲቀርብ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ሃብት ልማት ቡድን መሪ ሁሴን ሀሰን በ2017 ዓ.ም በዶሮ እና በከብት እርባታው ዘርፍ አበረታች ውጤት መታየቱን አረጋግጠዋል። ወጣቶችን በኢንተርፕራይዝ በማደራጀት የሥራ ዕድል እየተፈጠረላቸው እንደኾነም አቶ ሁሴን ተናግረዋል። ከቦታ ማስፋፊያ እና ከገበያ ትስስር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታትም አሥተዳደሩ በክላስተር መልክ ቦታ ለማዘጋጀት እየተሠራ ሲኾን ከዞኑ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ጋር በመተባበር የገበያ ትስስር ችግሩን ለመቅረፍ መታቀዱን አቶ ሁሴን አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን