
ጎንደር: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሠራተኞቹ በተለያዩ ምክንያት ደም ፈሷቸው ለህልፈት የሚዳረጉ ወገኖችን ለመታደግ ደም ለግሰዋል። ሰራተኞቹ በተጨማሪም የቀይ መስቀል አባልነታቸውንም አረጋግጠዋል።
የበጎ አድራጎት ሥራ ከውስጥ ፍላጎት የሚመነጭ እና ርካታን የሚፈጥር ነው ያሉት የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105 ነጥብ 1 ራዲዮ ጣቢያ ዋና አዘጋጅ እመቤት ሁነኛው እንደ ጋዜጠኛ ደም ሲለገስ ከመዘገብ ባለፈ የአሚኮ 30ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ደም መለገሳቸውን ገልጸዋል።
የጣቢያው ሁሉም ሠራተኞች የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አባል መኾን ችለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የአሚኮ 30ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በማኅበራዊ አገልግሎት ላይ መሳተፍ መቻላችን የማኅበረሰቡ አንድ አካል መኾናችንን ያሳያልም ብለዋል። የሰሜን ጎንደር ዞን ቀይ መስቀል ማኅበር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አታለል ታረቀኝ ተቋማቸው ገቢ የሚያገኘው ከአባላት ከሚሰበሰብ ገንዘብ መኾኑን በማንሳት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሁሉም ሠራተኞች አባል በመኾናቸው ምስጋናን አቅርበዋል። ኀላፊው አክለውም ቀይ መስቀል በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ለማኅበረሰቡ ከማሳወቅ እና ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ክፍተት አለብን እና ለወደፊቱ ከአሚኮ ጋር አብረን በመሥራት የበጎ ፈቃድ ተግባራትን እናከናውናለን ብለዋል።
ዘጋቢ:- ማኅደር አድማሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!