
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰማይ ባለቤት ወዷታል፤ ከሰማየ ሰማያት ኾኖ መርጧታል፤ ሰማያት ያከብሯታል፤ ደስም ይሰኙበታል፤ ምድርም ታመሰግናታለች፤ የጌታዬ እናት ትላታለች። ስሟን ታከብራለች።
ነብያት ተተነበዩልሽ፤ መላዕክት እህታችን እያሉ አመሠገኑሽ፤ ቅዱሳን ተመኩብሽ፤ ሐዋርያት አብዝተው ወደዱሽ፤ ደቀመዛሙርት በስምሽ የዕለት እንጀራቸውን አገኙብሽ፤ የዓመት ልብሳቸውን አፈሩብሽ። የተቸገሩ ጠገቡብሽ፤ የተጠሙ በስምሽ ጠጡብሽ፤ የታረዙ ለበሱብሽ፤ ያዘኑ ተረጋጉብሽ፤ ያለቀሱ ተጽናኑብሽ እያሉ ያመሠግኗታል። ከምድር እስከ ሰማይ የተዘረጋች መሰላል የተባልሽ፤ ትህትናን የታደልሽ፤ በንጽሕና የታተምሽ፤ በድንግልና የጸነስሽ፤ በድንግልና የወለድሽ፤ በድንግልና የኖርሽ፤ መላዕክት ክንፋቸውን ዘርግተው የሚያመሠግኑሽ ቅድስት ኾይ እያሉ ውዳሴ ያቀርቡላታል።
የማይወሰነውን የወሰንሽ፤ የማይቻለውን የቻልሽ፤ አንቺ የሕይወት ውኃ የፈለቀብሽ ምንጭ ነሽ፤ አንቺ የዓለም መድኃኒትን ያስገኘሽ የመድኃኒት እናት ነሽ፤ አንቺ የዓለም ብርሃን የወጣብሽ እመ ብርሃን ነሽ እያሉ ያመሠግኗታል ቅድስት ድንግል ማርያምን። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ታስተምራለች። በስሟ መታሰቢያን ታደርጋለች። በስሟ አብያተክርስቲያናትን ታንጻለች። በእርሷ ስም የተሰየሙ አጽዋማትን ትጾማለች። ከአጽዋማቱ መካከል ደግሞ ፍልሰታ አንደኛዋ ናት። በጾመ ፍልሰታ የቤተክርስቲያን ደወሎች በሌሊት ይደወላሉ። ካህናቱ ኑ ወደ እግዚአብሔር ቤት እያሉ ይጣራሉ። ሕጻናት በአብያተክርስቲያናት አጸድ ሥር ይሠባሠባሉ። ባሕታውያን ባዕታቸውን ይዘጋሉ። ደጋጎቹ በአርምሞ ይወሰናሉ።
መነኮሳት ሱባኤ ይገባሉ። ሊቃውንቱ ከእንቅልፍ ተለይተው በቤተ ክርስቲያን ለምሥጋና ይቆማሉ። ምዕምናን ነጫጭ እየለበሱ በሌሊት ወደ አብያተክርስቲያናት ለምሥጋና ይገሰግሳሉ። በፍልሰታ የቤተክርስቲያን አጽዶች በሰዎች ይሞላሉ። ፍልሰታ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ በጉጉት ትጠበቃለች። ሕጻናቱ ይናፍቋታል፣ አረጋውያን ይጓጉላታል። ዓመት እስኪያደርሳቸው ድረስ ይቸኩሉላታል። በፍልሰታ አቅማቸው ያልጸና ሕጻናት ኪዳን ሳያስደርሱ፣ ቅዳሴ ሳያስቀድሱ ምግብ አይቀምሱም። ይህም ለድንግል ማርያም ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹበት ነው። እነኾ ፍልሰታ ናትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተክርስቲያናት በሰዎች ተሞልተው ሰንብተዋል። በምሥጋና እና በውዳሴ ጸንተው ቆይተዋል። ዛሬ ደግሞ ዓመት እስኪደርስ ድረስ የሚናፍቋትን፣ የሚጓጉላትን፣ የሚወዷትን፣ በአንድነት በቤተክርስቲያን አጽድ ሥር የሚሠባሠቡባትን ፍልሰታን ይፈጽማሉ። ዛሬ የቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገት ያስባሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየረር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የትርጓሜ መጻሕፍት መምህር መላከ ታቦር ኃይለኢየሱስ ፈንታሁን የፍልሰታን ጾም ለመጀመሪያ ጊዜ የጾሟት ሐዋርያት ናቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ፍልሰታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትጾማለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ስለ አዕማደ ምስጢራት ሲማሩ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ይማራሉ፣ ስለ ድንግል ማርያም ያውቃሉ ይላሉ። አምስቱ አዕማደ ምስጢራት የቤተክርስቲያን መሰሶዎች ናቸው፤ ምስጢራት ሲነገሩም ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ይነገራል ነው የሚሉት። ኦርቶዶክሳውያን ከእግዚአብሔር ቀጥለው ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ይማራሉ፤ የኢትዮጵያ እና የቅድስት ድንግል ማርያም ግንኙነት ደግሞ የላቀ ነው፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ልጇ መሬቷን ዕርስት፤ ሕዝቧን አስራት አድርጎ ሰጥቷታል። በዚህም ኢትዮጵያውያን ማርያምን አብዝተው ይወዷታል ነው የሚሉት።
በኢትዮጵያ ምድር የቅድስት ድንግል ማርያም አብያተክርስቲያናት ከሁሉም ይልቃሉ። ሕጻናት ፊደል ሲቆጥሩ ሀ ግዕዝ ብለው እንደሚጀምሩ ሁሉ ጾምም የሚጀምሩ በፍልሰታ ነው ይላሉ። ማርያም የሕጻናት የአፍ መፍቻቸው የጾም መጀመሪያቸው፤ ርህርሂት እናታቸው ናትና ሕጻናት አብዝተው ይወዷታል ይላሉ። ሊምረው የወደደውን የድንግል ማርያምን ፍቅር ያሳድርበታል እንዳሉ ሊቃውንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞችን ከድንግል ማርያም ነጥሎ ማየት አይቻልም እነርሱ አብዝተው ይወዷታል፤ ይተማመኑባታልም ነው የሚሉት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለድንግል ማርያም የተለየ ፍቅር አለው። ኢትዮጵያውያን ሊቃውንቱ ጽፈውላታል። አዚመውላታልም ይላሉ።
እናቶች ሊወልዱ ምጥ ሲያዙ አረጋውያን ተንበርክከው ማርያም ነይላት እያሉ ይማጸናሉ፣ የለወደችን እናት ለመጠየቅ ሲገቡ እንኳን ማርያም ማረችሽ፣ ሲወጡም ማርያም በሽልም ታውጣሽ ይላሉ፣ ሕጻናት ባያውቁም ገና ሲወለዱ ጀምረው የማርያምን ስም ይሰማሉ ነው የሚሉት። በልጅነት ስሟን የሰሟት ሕጻናትም ነፍስ ባወቁ ጊዜ በፍልሰታ ስሟን እየሰሙ በቤተክርስቲያን አጸድ ሥር ይሠባሠባሉ። ሕጻናት ፍልሰታን የሚናፍቋትም የድንግል ማርያም ፍቅር ከአዕምሯቸው ሰለማይለይ ነው ይላሉ። ማተብ ያሰረ ሁሉ ፍልሰታን ይጾማል። ይህ ደግሞ ከፍቅሯ የተነሳ ነው። ጾምም የመታዘዝ እና የፍቅር መገለጫ ነው። ማተብ ያሰረ ሁሉ የፍልሰታ ጾምን የሚጾም ፍቅሩን ለመግለጽ ነው ይላሉ።
በፍልሰታ የሚገለጥ ፍቅር እና መታዘዝ ለሀገር ሰላምም መሠረት ነው። ሰው ከሃይማኖት ከወጣ ለሀገር አይሆንም፣ ሰው እግዝአብሔርን ሲፈራ ሀገርን ይጠቅማል፣ በሰማይ እግዚአብሔርን፣ በምድር ሀገርን ያልወደደ ሰው ሰው አይደለም ነው የሚሉት። እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው አንድነትን ይወዳል። መለያየትን ይጸየፋል። ጠብ እና ግጭትን ይርቃል ነው የሚሉት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም በቅዳሴዋ ለሀገር ሰላምን ስጣት፤ ጠላቶቿን ከእግሯ በታች አስገዛላት፤ ሕዝቧን፣ ሠራዊቷን፣ ሃይማኖቷን ጠብቅ እያለች ትጸልያለች ነው ያሉት። ሰዎች ጨካኞች የሚኾኑት ከሃይማኖት ሲርቁ ነው። ከሃይማኖት ሲርቁ ከምግባር ይርቃሉ። ከምግባር ሲርቁም ጨካኞች ይኾናሉ ነው የሚሉት።
በኢትዮጵያ ሕጻናት ላይ የሚጨክኑ፣ ሕጻናትን የሚያግቱ የተፈጠሩት ከሃይማኖት እና ከሰውነት ስለራቁ ነው ይላሉ። በሕጻናት ላይ የጨከነ ወዮለት ቅጣቱ የከፋች ናት ነው የሚሉት ሊቁ። ጭካኔ የሚጠፋው ሰዎች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው እግዚአብሔርን መፍራት ሲጀምሩ ነው ይላሉ። እነኾ በፍልሰታ የመጨረሻ ቀን በማርያም ዕርገት አማኞች በቤተክርስቲያን አጽድ ሥር ተሠባሥበው ኢትዮጵያን ሰላም ስጣት፤ ልጇቿን አፋቅርላት፤ የጭንቅ እና የመከራን ዘመናት አርቅላት እያሉ እየተማጸኑ ነው። ዓመት ታደርሳቸው ዘንድ አደራ እየሰጧት ነው። የመከራ ዘመናት፣ የግጭት እና የጦርነት ጊዜያትም እንደሚያልፉ፣ ፍቅርም በምድሯ ላይ እንደምትደረጅ፣ ቀናት፣ ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራትም ዓመትን ሞልተው ከሚናፍቋት ፍልሰታ በሰላም እንዲደርሱ ተስፋቸው የጸናች ናት።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን