
አዲስ አበባ: ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ ተገንብተው የተጠናቀቁ የገበያ ማዕከላትን እና የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክቶችን መርቀዋል። በ2017 በጀት ዓመት በመዲናዋ 19 ሺህ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን ከንቲባዋ አንስተዋል።
በመዲናዋ የገበያ ማዕከላትን እና የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን በማስፋት የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል። ከሜክሲኮ እስከ ለገሃር 13 የሚኾኑ የመኪና ፓርኪንጎች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል ነው ያሉት። በአንድ ጊዜ ብቻ ከ2 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም እንዳላቸውም ገልጸዋል። በተጨማሪም አስር ተርሚናሎች ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን ጠቁመዋል። ይህም በአንድ ጊዜ ብቻ ከ1 ሺህ 600 በላይ ተሽከርካሪዎችን እንደሚዝ ተናግረዋል። ከአሁን በፊት በከተማዋ በቂ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች ባለመኖራቸው ከፍተኛ የኾነ የትራፊክ መጨናነቅ ችግር እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ አሁን ላይ የተገነቡት የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክቶች የትራፊክ ፍስሰቱን በማሳለጥ ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።
በመዲናዋ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ከኾኑት የገበያ ማዕከላት መካከል የስኬት እና የአፍሪካ ኅብረት የገበያ ማዕከላት ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ የገበያ ማዕከላት የከተማውን ኢኮኖሚ በማነቃቃት እና የተለያዩ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ በማቅረብ እንድሁም የሥራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ ሚናቸው የጎላ መኾኑን ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የገለጹት። የአካባቢውን ማኅበረሰብ አቅም ባገናዘበ ሁኔታ ምርትን ከማቅረብ በተጨማሪ ምቹ የግብይት ምኅዳር እንዲኖር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸውም ተናግረዋል። ለአገልግሎት ክፍት የኾኑት ፕሮጀክቶች የካፍቴሪያ፣ የመዝናኛ፣ የሱቅ አገልግሎት፣ የመጸዳጃ ቤቶች፣ ዘመኑን የዋጁ የደኅንነት ካሜራዎች እና ሌሎች ቴክኖሎጅዎችን ያሟሉ ናቸው። በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መልክ የሚያሳዩ እና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያረጋግጡ ስለመኾናቸውም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!