እኛስ ያጣነውን ሰላም ለመመለስ ስንት ዓመታትን እናልቅስ?

18
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ በጉጉት ከሚጠበቁ አጽዋማት መካከል አንዷ ናት ጾመ ፍልሰታ፡፡
ፍልሰታን ከሕጻናት እስከ አዛውንት፣ ከመኳንንት እስከ ሊቃውንት በየዓመቱ ወርሐ ነሐሴ መጀመሪያ ቀን በትዝታ ተቀብለው በወሩ አጋማሽ ላይ በትውስታ ይሸኟታል፡፡ የሃይማኖቱ ተከታዮች ሁለቱን ሳምንታት በአብያተ ክርስቲያናት ተሰባስበው በጾም፣ በጸሎት፣ በአምልኮ፣ በስግደት፣ በውዳሴ፣ በቅዳሴ ያሳልፏታል፡፡ ፍልሰታ ማለት ከዚህኛው ዓለም ወደዚያኛው ዓለም መሸጋገር ማለት እንደኾነ የነገሩን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ መምህር እና አማካሪ የኾኑት መምህር ገብረ ጊዮርጊስ “ፍልሰቷ” ተብሎ በሴት አንቀጽ የቀረበ መኾኑን ያነሳሉ፡፡ ፍልሰታ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 15 ቀን ድረስ ተጹሞ ነሐሴ 16 ቀን የድንግል ማርያምን እርገት ተከትሎ የሚከበር በዓል ነው ይላሉ፡፡
“ሞት በጥር፣ በነሐሴ መቃብር ለሰሚም አያምር” እንዳለ ቅዱሱ ቶማስ ጾመ ፍልሰታ በሐዋርያት ዘንድ ሁለት ጊዜ እንደተጾመ መምህር ገብረጊዮርጊስ ይናገራሉ፡፡ የመጀመሪያው በድነ ስጋዋን ፈልገው የገቡት ሱባኤ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ ሐዋርያት ቶማስ ትንሳኤሽን አይቶ እኛ ሳናይ ብለው የጾሙት ጾም ነው ይላሉ፡፡ ያፈለጉትን ለማግኘት እና ያጡትን ለመመለስ ሱባኤ መግባት ከሐዋርያትም ቀድሞ ነበር፡፡ እስራኤል ዘስጋ እጅግ የሚወዱት ነብዩ ሙሴ ከዚህ ዓለም ድካም ድንገት አረፈባቸው፡፡ ወዳጆቹ እና ተከታዮቹ ታላቁን ነብይ ገንዘው አልቀበሩትም፡፡ ጭራሹን መቃብሩን እንኳን አያውቁም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ልባቸው በሐዘን የተሰበረባቸው እስራኤላውያን ለሊቀ ነብያት ሙሴ 30 ቀናትን ሙሉ መታሰቢያ አድርገው አለቀሱ፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያምም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት የገጠማቸው እንዲህ ያለ የልብ ስብራት ነበር ይላሉ መምህር ገብረ ጊዮርጊስ፡፡ ሐዋርያት ድንግል ማርያምን በእለተ ሞቷ አልቀበሯትም ነበር፡፡ በዚህም ሐዋርያት አዝነዋል፡፡ እርሷን ያዩ ዘንድም ሱባዔ መያዝን ወደዱ
ከመጀመሪያው ሱባኤ በኋላ ሥጋዋ ተሰጥቷቸው ቀበሯት፡፡ በልጇ ክርስቶስ ሥልጣን ተነሳች፡፡ የቀበሯት ሐዋርያት ትንሳኤዋ አላዩም ነበር የሚሉት መምህር ገብረ ጊዮርጊስ ያልቀበራት ቶማስ ግን ትንሳኤዋን አየ፡፡ ከፈኗን አሳይቶ መነሳቷን ነገራቸው በዓመቱም ሌላ ሱባኤ ያዙ ይሉናል፡፡ ሁለተኛውን ሱባኤ ሲያጠናቅቁ ትንሳኤዋን አዩ፡፡ ፍልሰታ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከዚህኛው ዓለም ወደዚያኛው ዓለም ሽግግር የታየባት ጾም ነች ብለውናል፡፡
ፍልሰታ በሐዋርያት ዘንድ ለሰማይ እና ለምድር የከበደ ታላቅ ደስታን ያዩበት በዓል ነው የሚሉት መምህር ገብረ ጊዮርጊስ በአስራት ሀገሯ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በቅን ልቦና በንፁሕ ሕሊና በየዘመኑ የሚያጋጥሙንን የሰላም እጦት እና ችግሮች ልንሻገር ይገባል ይላሉ፡፡ የሰው ልጅ ለራሱ የሚፈልገው ሁሉ ለወንድሙም እንዲኾንለት መመኘት እና መሻት ይኖርበታል ያሉት መምህሩ በእኛ ላይ እንዲፈፀም የማንፈልገውን ሁሉ በሌሎች ላይ እንዲፈፀም መፍቀድ አይኖርብንም ነው ያሉት፡፡ ሐዋርያት ያረፈ ስጋዋን ሽተው እና ትንሳኤዋን መመልከት ተመኝተው ሰባኤ ገቡ፤ የልባቸው መሻት ኾነላቸው፤ እኛስ ያጣነውን ሰላም ለመመለስ ስንት ዓመታትን እናልቅስ?
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአሚኮ በማኅበራዊ ዘርፍ ውጤታማ ሥራ ሠርቷል፡፡
Next articleበ2017 በጀት ዓመት በመዲናዋ 19 ሺህ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።