መድኃኒትን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መውሰድ ምን ሊያስከትል ይችላል ?

10
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለሥልጣን መድኃኒቶች በሽታን ለመፈወስ፣ ለማስታገስ፣ ለመከላከል፣ የሕመም ምልክቶችን ለመቀነስ፣ በሽታዎችን ለመመርመር የሚያገለግሉ ኬሚካሎች ወይም ውህዶች እንደኾኑ ይገልጻቸዋል።
በጤና አጠባበቅ ሥርዓት ውስጥ አስፈላጊ ከኾኑት ግብዓቶች ውስጥም ዋነኛዎቹ እንደኾኑ ያትታል። መድኃነቶች ለማኅበረሰቡ ጥቅም እንዲሠጡ ፈቃድ ከተሰጣቸው በኋላ በአግባቡ እንዲወሰዱ ይመከራል። በአግባቡ ካልተወሰዱ በተለይም ደግሞ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ከተወሰዱ ለተለያዩ ችግሮች የማጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ ይኾናል። መድኃኒቶችን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መውሰድ ሊያሳድሩት የሚችሉት ተጽዕኖ ምን እንደሚመስል የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት ከኾኑት ዶክተር መኮንን አይችሉህም ጋር ቆይታ አድርገናል።
ዶክተር መኮንን በማኅበረሰቡ ዘንድ መድኃኒትን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የመውሰድ ልምድ ይታያል ብለዋል። በእርግጥ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ መድኃኒቶች እንዳሉም ባለሙያው ገልጸዋል። እነዚህ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ሊሰጡ የሚችሉ መድኃኒቶች በማንኛውም ሕጋዊ ሰውነት ካላቸው መድኃኒት ቤቶች የሐኪም ትዕዛዝ ወረቀት ሳያስፈልግ ሰዎች በቀጥታ ገዝተው ሊጠቀሟቸው የሚችሉ ናቸው ነው ያሉት። በዓለም ላይም ከ100 ሺህ እስከ 300 ሺህ መድኃኒቶች ያለ ማዘዣ እንደሚወሰዱም ነው የገለጹት። ከእነዚህ መድኃኒቶች መካከል የሕመም ማስታገሻ፣ የተለያዩ ዓይነት ቫይታሚኖች፣ የወሊድ መከላከያዎች፣ የሳል ሽሮፖች፣ ቅባቶች እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ ብለዋል።
በመድኃኒትነት ከሚታዘዙት ውጭ እንደ ምግብ የሚወሰዱ መድኃኒቶችም ያለማዘዣ ሊወሰዱ እንደሚችሉም ገልጸዋል። ታዲያ እነዚህም ቢሆኑ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ መድኃኒቶችን ያለ ባለሙያ ትዕዛዝ በመውሰድ ለከፋ ችግር እየተጋለጠ መኾኑንም ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ በተከሰቱት ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት አመጣጣቸው የማይታወቁ፣ በሕገ ወጥ መንገድ የሚገቡት እና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ጭምር በመግዛት የመጠቀም ነገሮች እየተስተዋለ ይገኛል ብለዋል።
መድኃኒትን ያለ ባለሙያ ትዕዛዝ መውሰድ በሰው ጤና ላይ በተለይም ደግሞ እንደ ካንሰር እና ለመሳሰሉ በሽታዎች በማጋለጥ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጫና ያደርሳሉ ነው ያሉት ዶክተር መኮንን። የመድኃኒት መላመድም ያስከትላል። ለሕይወት መጥፋትም ምክንያት እየኾኑ ይገኛሉ ብለዋል። ከዚህ በፊት የጤና አጠባበቅ ትምህርት ለማኅበረሰቡ በመስጠት ችግሩን መቀነስ ቢቻልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጸጥታው ችግር ምክንያት እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ችግሩ አሳሳቢ እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ ወጣቶች፣ መድኃኒት ያለ ባለሙያ ትዕዛዝ መውሰድ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች፣ የመድኃኒት እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የጉዳቱ ሰለባ ናቸው ነው ያሉት።
ተገቢ የሕግ ቁጥጥር በሌላቸው አካባቢዎች ደግሞ በየቦታው መድኃኒት ከሌሎች እቃዎች ጋር ቀላቅሎ ለማኅበረሰቡ የማሠራጨት ችግር እንደሚታይም አንስተዋል። ማንኛውም ዓይነት መድኃኒት በሚወሰድበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የተናገሩት ዶክተሩ የመጀመሪያው ከመድኃኒት አቀማመጥ የሚጀምር ነው። መድኃኒቶች የራሳቸው የኾነ የአቀማመጥ ሥርዓት እንዲኖራቸው ይጠበቃል። ምክንያቱ ደግሞ በአቀማመጥ ስህተት የተነሳ መድኃኒቶች ሊሰጡ የሚገባቸውን ጥቅም ሊቀንስ ወይም ጨርሶ ሊታጣ ይችላልና ነው ያሉት።
ለምሳሌ መድኃኒቶች ለፀሐይ ብርሃን ሲጋለጡ ወይም ከፍተኛ የሆነ ሙቀት ባለበት ቦታ ሲቀመጡ ባህሪያቸውን ስለሚቀይሩ በመድኃኒቶች ማሸጊያቸው ላይ የተቀመጡ የአቀማመጥ መመሪያዎችን መከተል፣ የመድኃኒት ቤት ባለሙያን ማማከር ተገቢ ነው ብለዋል። የመድኃኒት ቤት ባለሙያዎችም ጉዳዩን ለተጠቃሚዎች ሊያስረዱ ይገባል ነው ያሉት። ከዚህ በተጓዳኝ በተለምዶ ለሕመም ማስታገሻነት ተብለው የሚወሰዱ መድኃኒቶች መጠን እና ድግግሞሽ በበዛ ቁጥር ኩላሊትን ጨምሮ በተለያየ አካል ክፍል ላይ ጫና ሊፈጠር ይችላል። መድኃኒቶች ተወስደው የሚጠበቀው ለውጥ ካልታየ ሐኪምን ማማከር ተገቢ እንደኾነ ገልጸዋል።
ሐኪም ያዘዛቸው መድኃኒቶች አወሳሰድ ላይም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። መድኃቶችን ማቋረጥ፣ በተገቢው ሰዓት አለመውሰድ፣ መድኃኒቱ የሚፈልገውን ያህል በቂ ፈሳሽ አለመጠቀም ከሚታዩ ክፍተቶች መካከል ናቸው። በመድኃኒት አጠቃቀም ላይም ለማኅበረሰቡ ዘላቂ ትምህርት መስጠት እንደሚያስፈልግ መክረዋል። ለዚህ ደግሞ ከጤና ተቋሙ ባለፈ የሁሉም ተቋማት ጉዳይ ኾኖ ሊሠራ ይገባል ብለዋል። ከዚህም ባለፈ በሥርዓተ ትምህር ጭምር አካቶ በተደራጀ መንገድ ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ የኅብረተሰቡን የጤና ችግር መፍታት መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“የሚናፈቅ ውበት፣ የኖረ ማንነት”
Next articleበሰሜን አሜሪካ እና ካናዳ የሚደረገውን የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ ለማከናወን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።