
ባሕር ዳር: ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ነሐሴ በዋግኽምራ ልዩ መልክ አላት። ጋራ እና ሸንተረሩ አረንጓዴ ይለብሳሉ፤ ከአረንጓዴውም መካከል የሻደይ ቅጠሎች ዘለላ ከምድሩ እና ከሰዎቹ ታሪክ ጋር ጎልተው ይታያሉ።
“አስገባኝ በረኛ – የጌታዬ ዳኛ፣
አስገባኝ – ከልካይ እመቤቴን ላይ…” እያሉ የሚያዜሙ፣ በእምነት፣ በባሕል፣ በእሴት እና በውበት የደመቁ የዋግ ልጃገረዶችን በነሐሴ ወር ማየት እንግዳ ትዕይንት አይደለም።
ሕብረ ዝማሬው፣ የሴቶቹ ውበት፣ አጊያጊያጥ እና አለባበሳቸው ዐይን፣ ጆሮ እና ቀልብን በመያዝ ነሐሴን በሙሉ ከዋግሹሞች ጋር መክረምን ያስመኛሉ። በአሽኩቲና ናትራ በታሸ ቂቤ ተነክሮ ያማረ ቀሚስ የለበሱ፣ ሎሚ ተረከዛቸውን በጥልፍልፍ ጫማ ያሰሩ፣ ክንዳቸው ላይ ከብር የተሠራ አምባር እና ድኮት ያጠለቁ ልጃገረዶች ከነሐሴ ጋር ቀጠሯቸው የጠበቀ ነው። በወርሐ ነሐሴ ወደ ዋግሹሞች ቀዬ የዘለቀ እንግዳ መቃ አንገታቸውን በድሪ እና ብር መስቀል ያስዋቡ፣ ጸጉራቸውን በቀዬው ወግ መሠረት አስተካክለው የተዋቡ እና ሻደይ ቅጠል በወገባቸው ዙሪያ አስረው በጭፈራው መሀል እንደ እንዝርት የሚሾሩ ባለአረንጓዴ ክንፍ ርግብ መሳይ ሴቶችን አይቶ፣ በባሕል እና እሴታቸው ይደነቃል።
ነሐሴ ሲጋመስ የዋግ ጋራና ሸንተረሮች ከልጃገረዶች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ባለው የሻደይ ቅጠል ያሸበርቃሉ። ቀዬው ሁሉ በወይዛዝርቱ ዝማሬ፣ በቆነጃጅቱ ፍልቅልቅ መልክ እና በጎበዛዝቱ እጀባ ይደምቃል። የቤተ ክርስቲያን አጸዶች ሁሉ የሻደይ ቅጠል በወገባቸው ዙሪያ ባሠሩ ሴቶች ዝማሬ፣ በቀሳውስቱም ምርቃት ይሞላሉ። በየዓመቱ ከነሐሴ 16 እስከ 21 በዋግ ያለው የሻደይ ትዕይንት በአካል ተገኝተው ዐይን እስኪፈዝ የሚያዩት፣ የእውነት ሀሴትም የሚሸምቱበት እንጅ “እንዲህ ነው” ብለው በመጻፍ እና በመናገር ሊገልጹት የማይችል ጥልቅ ውበት ነው።
የሻደይ ክዋኔው ባሕልን ከእምነት እና ከእሴት ጋር ያጋመደ እንደኾነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዋግኽምራ ሀገረ ስብከት የወለህ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ጉባኤ ቤት የመጻሕፍት መምህር መዝገበቃል ገብረሕይወት ያስረዳሉ።
ሻደይ በተለይም ከሴቶች ጋር የተያያዘ በዓል ነው። ይህም ከድንግል ማርያም እርገት ጋር የሚያያዝ ሃይማኖታዊ መሠረት አለው ነው ያሉት። መላዕክት በደስታና በዝማሬ እንዳሳረጓት ሁሉ ሴቶችም በዚህ በዓል ይሄንን ያወሳሉ ብለዋል። ልጃገረዶች በዓሉን ቀን ወደ ተራራ ወጥተው ሻደይ ይለቅማሉ፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን በማምራትም ይሳለማሉ፤ ይባረካሉ፤ ዝማሬና ሽብሸባም ያደርሳሉ ነው ያሉት መምህሩ። ሻደይ እምነትን ከባሕል እና ከእሴት ጋር አሰናስሎ እንደሚከበርም ገልጸዋል። ተዝቆ ከማያልቀው የሻደይ ትዝታዋ ያጋራችን የዝቋላ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ምሥራቅ ወለደ ሻደይ በተለይም ለሴቶች የነጻነት፣ የውበት፣ የባሕል፣ የእሴት እና የእምነታቸው መገለጫ ተናፋቂ በዓል ነው። የበዓሉን አከባበር እና ሁነቶችንም ነግራናለች።
ሴቶች በሦስት የእድሜ ደረጃ ማለትም ሕጻናት፣ ወጣቶች እና እናቶች ተብሎ በመከፋፈል እንደየእድሜ ደረጃቸውም የተለያየ አለባበስ እና አጊያጊያጥን በመከተል የሚያከብሩት ነው። ሕጻናት መሀል ራሳቸው ላይ የሚኾነውን ጸጉራቸውን ይላጫሉ፤ ይህም ጋሜ ይባላል። ወጣቶች ደግሞ የበለጠ ውብ ኾኖ ለመታየት በሚያስችል አኳኋን ጸጉራቸውን ወደ ኋላ እና በቀጭን ተጎንጉነው የበለጠ አሳምረው ይሠሩታል።
ከአንገታቸው ከላይ እና ከታች የሚኾኑ ሁለት የብር መስቀሎችም ያሠራሉ። ከላይ ያለው ብር መስቀል አነስ ያለ ሲኾን ከታች የሚታሰረው ደግሞ ተለቅ ያለ ነው። በሁለቱም እጃቸው ላይም የሚያደምቃቸውን ድኮት ወይም አምባር ያጠልቃሉ ብላናለች ወይዘሮ ምሥራቅ።
እናቶች ደግሞ የጸጉራቸውን ዙሪያ በቀጭን በመጎንጎን ትንሽ ወረድ አድርገው ዙሪያውን ያስሩታል። መሀሉን ደግሞ በቀጭኑ ወደ ኋላ ይጎነጉኑታል። ይህም የእናቶች ጸጉር አሠራር “ድርምም” ይባላል። በዚህ መልኩ ያጌጡ ሴቶች በተለይም ልጃገረዶች የሻደይ ቀን በጠዋት ይወጡና ተጠራርተው ለሻደይ ቅጠል ለቀማ ወደ ጋራና ሸንተረሮች ይወጣሉ። በሻደይ ዝማሬዎች ታጅበው ቅጠሉን ከለቀሙ በኋላ ለየወገባቸው በሚመች መልኩ ይጎነጎናል። ወይዘሮ ምሥራቅ እንደነገረችን በተለይም ነሐሴ 16 የኪዳነ ምሕረት ቀን በጠዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመራሉ። በዚያው ተሳልመው ሥርዓተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ ባለአረንጓዴ ክንፍ ልጃገረዶች ደጀ ሰላሙን እየዞሩ ጣዕመ ብዙ ዝማሬዎችን ያስተጋባሉ።
“ሻደይ- ሎሚ ለወ…” እያሉ ያዜማሉ፤ ቀሳውስቱም ይመርቋቸዋል።
በመቀጠልም ወደ መኖሪያ ቤት ይዘልቃሉ።
“እንክት እንክት እንጅ የምን ግትር ግትር፣
ሰዎቹም እንዳይሉን የክትክታ በትር” እያሉ በማዜም እስክስታ የሚያወርዱ ልጃገረዶች አጥንት ያላቸው አይመስሉም።
ይሄኔ የወንዶች ሚና የአጃቢነት ነው። ሀጫ በረዶ ጥርሳቸው ላይ መፋቂያ የማይጠፋ፣ ጸጉራቸውን ያበጠሩ፣ ያማረ ቁምጣቸውን ያጠለቁ፣ በትራቸውን በትክሻቸው ላይ አግድም ያጋደሙ እና በኩራት የሚመለከቱ ወንዶች አይጠፋም። ሁሉም ወንዶች በፍቅር እና በስስት ነው የሚያዩት። ለትዳር የከጀሏትን እዚሁ ላይ መምረጥ ግን የወግ ነው። ከአቻ ጋር ትግል መግጠም፣ ክንድ መጨባበጥ እና መነጣጠቅ ደግሞ የወንድነት መለኪያ እና ከልጃገረዶች ዐይን የመግቢያ ዘዴ ነው። ወይዘሮ ምሥራቅ እንደምትለው ወጣት ወንዶች ልባቸው ወደ ከጀላት እየቀረቡ ከወገቧ ሻደይ ቅጠል ይመዛሉ። ሴቷ ፈቃደኛ ካልኾነች በዙሪያዋ ለሚንጎማለል ወንድሟ ወይም ቤተ ዘመድ ለኾነ ወንድ “እየረበሸኝ ነው” አይነት መልዕክት ታስተላልፋለች። ይሄኔ “እረፍ በነጻነት ትጫወት” ተብሎ በጨዋ ደንብ ይነገራል። ይህ ፈቃደኛ ያለመኾኗ መርዶ ነውና ቁርጡን ያውቃል፤ እጁንም ይሰበስባል። ሻደይ የተነቀለባት ልጃገረድ ለወጣቱ ፍላጎት ካላት ግን ፈገግታ ትቸረዋለች፤ ወደ መሀል ገብታ የበለጠ ጭፈራውን ታደራዋለች። ይሄኔ በጓደኞቹ መሀል እየተጎማለለ የመፈለጉን ብስራት በኩራት ይነግራል። ሻደይ ላይ የተጠነሰሰው ፍቅርም ወግ እና ማዕረጉን ጠብቆ፣ ሽማግሌዎች ተልከው ለጉልቻ የሚበቃ ይኾናል።
“አሽከር አበባዬ – አሽከር አበባ፣
አሽከር ይሙት ይሙት ይላሉ የኔታ፣
አሽከር አይደለም ወይ የሚኾነው ጌታ” እያሉ ለታላቅና ታናሹ ሁሉ ክብር እንደሚገባ የሚያሳብቁ ዝማሬዎችን ያዥጎደጉዳሉ።
አስገባኝ በረኛ – የጌታዬ ዳኛ፤
አስገባኝ – ከልካይ እመቤቴን ላይ…” በማለት በየበሩ ተገኝተው የዓመት ቀጠሯቸውን እና የአዲስ ዓመት ብስራት ዜማቸውን ያንቆረቁራሉ። በዚህ ጊዜ ሁሉም እንደየጸጋው ያለውን ያበረክትልናል ነው ያለችው ወይዘሮ ምሥራቅ። ማር እና ቂቤው ይዛቃል፤ ወተትም ይቀዳል፣ በጥሬ ገንዘብም የሚያበረክት አለ። የሚበላው ለፍቅር እና ለአብሮነት ማዕድ ይዘጋጃል፤ ጥሬ ገንዘቡ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ገቢ ይደረጋል ብላለች።
የሻደይ ቀናት ሲጠናቀቁ ቀጣይ ዓመት እስኪመጣ ይናፈቃል። የተያዘው ሻደይ ተጠናቅቆ የዓመት ቀጠሮ እስከሚደርስ መለያየት ግድ የኾነባቸው ልጃገረዶችም፦ “ሻደይ …ሻደይ – ኧረ እኛስ አንለይ” እያሉ በኅብረ ዜማቸው ይለያያሉ። እውነትም ተገናኝቶ ለመለያየት የሚቸግር፣ ዓመት ጠብቆ እስኪመለስ የሚናፍቅ ድንቅ በዓል!
መልካም የሻደይ፣ አሸንድየ እና ስለል በዓል ተመኘን!
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን