98 በመቶ የሚኾነው ማሳ በሰብል መሸፈኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።

10
ደብረማርቆስ፡ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ በ2017/18 የምርት ዘመን ከታቀደው ውስጥ 98 በመቶ የሚኾነውን ማሳ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈን መቻሉን አስታውቋል።
ዞኑ በዋነኝነት በጤፍ፣ ስንዴ እና በቆሎ ምርት ይታወቃል። በዚህ የምርት ዘመን ከ640 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳን ለማልማት አቅዶ ሢሠራ ቆይቷል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ እምቢአለ አለኸኝ እንደገለጹት እስካሁን ድረስ 98 በመቶ የሚኾነው የእርሻ መሬት በሰብል ተሸፍኗል። የምርት ዘመኑን ስኬታማ ለማድረግ እንደ “ኩታ ገጠም” ያሉ ዘመናዊ የአሠራር ዘዴዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
አርሶ አደሮችም የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ከባለሙያዎች ጋር በመተባበር ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። መምሪያው ለምርት ዘመኑ በቂ የአፈር ማዳበሪያ እና ከ23 ሺህ ኩንታል በላይ የተሻሻሉ የበቆሎ፣ የስንዴ እና የጤፍ ዘሮችን ማሰራጨቱን ገልጸዋል። በተጨማሪም የተዘራው ሰብል በአረም እና ተባይ እንዳይጠቃ የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች ተከታታይ ድጋፍና ክትትል እያደረጉም እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት። አርሶ አደሮች የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በመጠቀም የአፈር ለምነትን እንዲያሻሽሉም አሳስበዋል። በምርት ዘመኑ ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“ፈተናዎች ያልበገሩት፣ ችግሮች ያልገቱት”
Next article“ትምህርት ተሰደውም የሚፈልጓት ሃብት ናት”