
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በጤናው ዘርፍ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት ዶክተር መኮንን አይችሉህም ወደልጅነት የትምህርት ቤት ጊዜያቸው መለስ ብለው እንዲያወጉን ጋበዝናቸው። ዶክተሩ ምስጉን የጤና ባለሙያም ናቸው።
የዛሬው ዶክተር የያኔው ተማሪ ለወገናቸው ሕመም ፈውስ ሊኾኑ ብዕር እና ደብተር ያነሱት ወንድማቸውን ተከትለው ነበር። ውልደታቸው በጎጃም እነብሴ ሳር ምድር በተባለ አካባቢ የኾነው ዶክተር መኮንን ወደ 1963 ዓ.ም መለስ ብለው ሲያስታውሱ ወገናቸው ለትምህርት ያለው ፍቅር “ከምትገምተው በላይ ነው” አሉኝ። ወላጆች ሞልቶላቸው ትምህርትን ባይቀስሙም ልጆቻቸው በነሱው መንገድ እንዳያድጉ እና የዕውቀት ብርሃን ሳያገኙ እንዳይቀሩ ያደርጉት የነበረውን ጥረት ሲገልጹ “ብልህ እና አርቆ አሳቢ ሕዝብ” ይላሉ።
በእርሳቸው የልጅነት ጊዜ ዘመናዊ ትምህርትን እንዳሁኑ በተመቸ ጊዜ እና ቦታ ላይ ማግኘት አይቻልም ነበር ያሉት ዶክተሩ ከ1፡30 በላይ የእግር ጉዞ አድርገው ይማሩ እንደነበር ነው የነገሩን። “ትምህርትን ተሰደህ የምታገኛት ነበረች” ያሉት ዶክተር መኮንን በዚህ ውጣ ውረድ አልፈህ ለወገንህ መብራት እና አጋዥ ለመኾን ጠንክሮ መማር ይጠይቅ እንደነበር ይናገራሉ። “ትምህርት እንኳንስ በቀየ ተሰደውም የሚፈልጓት ሃብት ናት” የሚሉት ዶክተሩ በልጅነታቸው በችግር አልፈው ለማኅበረሰባቸው የነገ አገልጋይ እንደሚኾኑ ቀድሞ ይረዱ ነበር። ዘጠነኛ ክፍል ሲደርሱ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለማግኘት በብቸኝነት ትምህርት ይገኝበት ወደነበረው ሞጣ አውራጃ ማቅናታቸውን ያስረዳሉ።
በዛ ጊዜ ወላጆቻቸው ካላቸው ቀንሰው ቀለብ እየጫኑ እንዳስተማሯቸውም ተናግረዋል። በጊዜው ግን ልክ አሁን እንዳለው ሁኔታ ትምህርትን የሚያስተጓጉል ታሪክ መፈጠሩን አስታውሰዋል።
ከታሪካችን አልተማርንም፤ አሁንም ያለፈውን ስህተታችንን እየደገምን ነው ብለው የሚያስቡት ዶክተር መኮንን የንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ማብቃትን ተከትሎ ኢዲዩ፣ ኢሀፓ እና መሠል ድርጅቶች በሚል እርስ በእርስ በተፈጠረ ግጭት የትምህርት ጊዜ መባከኑን አስታወሱን። የቀደመ ታሪኩ ያላስተማረው ሕዝብ መለወጥ እና ማደግ ይቸግረዋል ነው ያሉት። ያ ዘመን እርሳቸው ከዕድሜአቸው የቀነሱበት እና ተምረው ወገናቸውን የሚጠቅሙ ሌሎች ልጆችም ከዓላማቸው የተደናቀፉበት፣ ማኅበረሰቡ እና ሀገርም የተጎዳበት ጊዜ እንደኾነ ጠቁመዋል። አሁንም ትምህርት ላይ ያልተማርንበትን ታሪካችንን እየደገምን ነው። ሁለት ዓመት ትምህርት መቋረጥ ማለት ምን ማለት እንደኾነ መገንዘብ ያስፈልጋል፤ ተምረው ሀገራቸውን ከበሽታ እና ከድህነት ሊያላቅቁ የሚችሉ ልጆችን እያጣን ነው ብለዋል።
የትምህርት ጉዳት የሚታወቀው በረጅም ጊዜ ሂደት ነው የሚሉት ዶክተር መኮንን ሁለት ዓመት ዩኒቨርሲቲ ገብተው ወገናቸውን በተማሩበት የሚጠቅሙ ልጆችን ማጣታችን ሊያስቆጨን ይገባልም ይላሉ። ምንም ልዩነት እንኳን ቢኖረን ትምህርት ላይ ቆም ብሎ አስቦ የትምህርት ሂደቱ እንዲቀጥል መተባበር ያስፈልጋል ነው ያሉት። መቸም ቢኾን ወገኑ እንዲጎዳ የሚፈልግ ባለመኖሩ የትምህርትን ጉዳይ አውጥጥቶ አውድዶ ማሰብ እና ተማሪዎች እንዲማሩ ማመቻቸት እንደሚገባም መክረዋል። “እኔ በመማሬ በተቻለኝ አቅም ወገኔን እየረዳው ነው” የሚሉት ዶክተር መኮንን የዛሬ ተማሪዎችም ዕውቀት የሚያገኙበት ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የተማረ ሰው ለችግሮች ሁሉ መፍቻ መንገድ እንደማያጣ የሚገልጹት ዶክተሩ ለትምህርት ከሁሉም ጉዳይ በይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት። በችግር አልፈው ወገናቸውን በትጋት እያገለገሉ የሚገኙት እኒህ ዶክተር 2012 ዓ.ም ላይ የጤና ሚኒስቴር “የሕይዎት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ተሸላሚ” በሚል ሸልሟቸዋል። የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሄልዝ ኢንስቲትዩትም በጤናው ዘርፍ ጥናት እና ምርምር ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ የሜዳሊያ ተሸላሚ አድርጓቸውም ነበር። እኒህ ችግርን አልፈው ለፍሬ የበቁ ዶክተር በዚህ ዓመት ትምህርት እንዲከፈት እና ተማሪዎች ወደዕውቀት እንዲመለሱ ሁሉም ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን