ከአማራ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት አምስት ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ማገገማቸውን ጤና ቢሮው ገለጸ።

284

በአማራ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 124 የላቦራቶሪ ምርመራ ሁሉም ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጿል።

በአማራ ክልል እስከ ዛሬ ሰኔ 1/2012 ዓ.ም ድረስ ለ3 ሺህ 155 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎ በ119 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ታውቋል። ከእነዚህ መካከል 28 ሰዎች አገግመዋል፤ እስካሁን በክልሉ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ ሰው አለመኖሩንም የጤና ቢሮው መረጃ ያመላክታል።

ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በክልሉ ለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከላት የሚገኙት ሁሉም ሰዎች በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውን፣ ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል የገባ ታማሚም አለመኖሩን ቢሮው በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ አስታውቋል።

እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ከምዕራብ ጎንደር ዞን (97) (ይህ አካባቢ ከሱዳን የሚገቡ ኢትዮጵያውያን በለይቶ ማቆያ የሚቆዩበት ነው)፣ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን (አንድ)፣ ከጎንደር ከተማ (ሦስት)፣ ከደሴ (ሁለት)፣ ከባሕር ዳር (አራት)፣ ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር (ሦስት)፣ ከሰሜን ሸዋ ዞን (ሁለት)፣ ከሰሜን ወሎ ዞን (አራት)፣ ከደቡብ ጎንደር ዞን (አንድ)፣ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር (አንድ) እና ከምሥራቅ ጎጃም ዞን (አንድ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ) መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ደግሞ እስከዛሬ ለ147 ሺህ 735 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፤ በአጠቃላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥርም 2 ሺህ 156 ደርሷል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 766 በሕክምና ላይ ይገኛሉ፤ 27 ሕይወታቸው አልፏል፤ 361 ደግሞ አገግመዋል፡፡ 32 ሰዎች በጽኑ ሕክምና ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

Previous articleበኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሚፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አስታወቁ፡፡
Next articleኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ሩሲያ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አሳወቀች፡፡