
ባሕርዳር፡ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ማሳያ ናቸው ብሏል።
ብዝኃነት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫዋ የኾነችው ኢትዮጵያ የክረምቱን መገባደድ የሚያበስሩ ትውፊቶች ባስቤት ናት። ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ልጀገረዶች ወደ አደባባይ በመውጣት የሚያሰሟቸው ኅብረ ዝማሬዎች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የክረምቱን መገባደድ፣ የጋራ ሸንተረሩን የአበቦች መፍካት፣ የምንጮችን መጥራት እና የቡቃያዎችን ማፍራት ያበስራሉ ነው ያለው። ከእነዚህ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች መካከል ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ለቀናት በድምቀት የሚከበረው እና በተለያዩ አካባቢዎች በተቀራራቢ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና አሸንዳ በሚሉ መጠሪያዎች የሚታወቀው በዓል ተጠቃሽ ነው ብሏል።
በዓሱ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ትውፊታዊ ዳራዎች በተቀራራቢ ዓውደ፣ በተመሳሳያ ጊዜ በተለያዩ ባሕላዊ ኅብረ ዝማሬዎች በሴቶች የሚከበር የነፃነት የአደባባያ በዓል ነው። ይህ በዓል የአጎራባች ሕዝቦች ግንኙነት እና ትስስርን በሚያገስብት መልኩ ማክበር፣ መጠበቅ እና ለትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል ነው ያለው በመግለጫው። ይህ በዓል ከትውልድ ትውልድ እየተወራረሰ ቢመጣም በአግባቡ ተዋውቆ አንድ የመስህብ ሃብት እንዲኾን ተጨማሪ ሥራ እንደሚያስፈልግ አመላክቷል።
ከዚህም ባሻገር ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚከበሩ የተለያዩ በዓላት ጋር በማስተሳሰር ኅብረ ብሔራዊነትን በሚገነባ መልኩ መሥራት ይጠይቃል ነው ያለው። የጳጉሜን ቀናት፣ የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት፣ የተለያዩ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት፣ የመስቀል በዓል እና የኢሬቻ በዓልን በቅርብ ርቀት የሚያስከትሉ በመኾናቸው የበለጠ ለጎብኝዎች ቆይታ መራዘም ጉልህ ሙና ሊጫወቱ የሚችሉ ናቸው ብሏል። በተለመደ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴታቸው መሠረት በድምቀት እየተከበሩ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርገል ነው ያለው በመግለጫው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን