
ሁመራ፡ ነሀሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ200 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅዶ እየሠራ መኾኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
ተማሪ ሀብታሙ ሰለሞን የማይካድራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ተማሪ ሀብታሙ በክረምቱ ሲናፍቀው ወደነበረው ትምህርቱ ለመመለስ ቀድሞ ተመዝግቧል። ባለፈው ዓመት ከ9ኛ ወደ 10ኛ ክፍል ከክፍሉ 2ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን ገልጾ በዚህ ዓመት ደረጃውን ለማሻሻል ማቀዱን ለአሚኮ ተናግሯል። የዘንድሮው ምዝገባ ቀድሞ መጀመሩ ትምህርቱ ላይ አስቀድሞ ትኩረት ማድረግ እንዲችል እንደሚያግዘው የገለጸው ተማሪ ሀብታሙ ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እያደረገ መኾኑንም አስረድቷል።
የማይካድራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አባተ ሞላ የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን በተሳካ ሁኔታ ለመፈጸም ከሚያስችሉ ተግባራት መካከል የተሳካ የተማሪዎች ምዝገባ ማድረግ አንዱ መኾኑን ተናግረዋል። ከላይ እስከታች ካለው የከተማ አሥተዳደሩ መሪ እና መዋቅር ጋር በመቀናጀት ተማሪዎችን በዕቅዱ ልክ ለመመዝገብ ታስቦ እየተሠራ ነው ብለዋል። የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ዮናስ ታደሰ በተያዘው የትምህርት ዘመን በወረዳው ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መኾኑን ለአሚኮ ተናግረዋል። ወረዳው ትምህርትን ተቀዳሚ ተግባር አድርጎ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ዮናስ የተያዘውን ዕቅድ ለመፈጸም ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ዞኑ አንጻራዊ ሰላም ያለበት በመኾኑ የመማር ማስተማር ሂደቱ ውጤታማ ሊኾን እንደሚችል ገልጸዋል። የማይካድራ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የንግድ እና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይለፍ ዘውዱ በከተማ አሥተዳደሩ በፓይለት ምዝገባ ቀናት የዓመቱን ዕቅድ የተማሪ ምዝገባ ለማከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል። በዚህም ሙሉው የከተማው መሪ ለተግባራዊነቱ አጋዥ እንዲኾን በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን ነው አቶ ይለፍ ያስረዱት። የክረምቱ የአየር ሁኔታ ፈታኝ ቢኾንም ምዝገባው በሁሉም ትምህርት ቤቶች በታቀደለት ልክ እየተከናወነ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ተማሪዎችን እና የትምህርት ባለድርሻ አካላትን ለማነቃቃት የሚያስችለው የፓይለት ምዝገባ በአንድ ወረዳ እና በሁለት ከተማ አሥተዳደሮች መጀመሩን የዞኑ ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ቡድን መሪ አስረሳ ወንድይፍራው ገልጸዋል። በቃብትያ ሁመራ ወረዳ፣ በዳንሻ እና በማይካድራ ከተማ አሥተዳደሮች የተጀመረው የፓይለት ምዝገባ ከተጠበቀው በላይ መኾኑንም ቡድን መሪው አንስተዋል።
ምዝገባ የተከናወነባቸው አካባቢዎች ጠንካራ የሕዝብ አደረጃጀት ያለባቸው በመኾኑ የተሻለ ንቅናቄ መደረጉንም አቶ አስረሳ አስረድተዋል። ቡድን መሪው በተያዘው የትምህርት ዘመን በዞኑ ከ200 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን