
ደሴ: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት መረጃ ለሕዝብ በማድረስ ለኅብረተሰብ ለውጥ ሲተጋ ቆይቷል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ደግሞ ተቋሙ አድማሱን እያሰፋ ሰድስት የሬዲዮ እና ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመክፈት ኅብረተሰቡን ሲያገለግል ቆይቷል።
ተቋሙ በሰሜኑ ጦርነት የንብረት ውድመት ከገጠሙት ተቋማት መካከልም አንዱ ነበር።በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ዘረፋ እና ውድመት ከደረሰባቸው ቅርንጫፎቹ ውስጥም አማራ ኤፍኤም ደሴ 87 ነጥብ 9 ሬዲዬ ጣቢያ አንዱ ነበር፡፡ በአካባቢያዊ ስርጭት እና በቅብብሎሽ ለማኅበረሰቡ ሁነኛ የመረጃ ምንጭ በመኾን የ24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የሬዲዮ ጣቢያው ያኔ ዘመናዊ የማሰራጫ መሳሪያዎቹ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡
ወድቆ የመነሳት፤ ለሐቅ ፀንቶ የመቆም ተምሳሌት የኾነው አሚኮ የደረሰበትን ጉዳት አድሶ በአዲስ ይዘት እና አቀራረብ እነሆ ዛሬ ላይ ከፈተና ማግስት ሁነኛ የመረጃ ምንጭ መኾኑንም ችሏል፡፡ አሚኮ ችግርን ተሻግሮ ዛሬ ላይ ከሬዲዮ ባሻገር በቴሌቪዥን ዜና እና ፕሮግራሞች ተደራሽነቱን ከፍ አድርጓል፡፡ አሚኮ ከውድመት እና ዘረፋ ማግስት በፈተናዎች ውስጥ እየተሻገረ ይበልጥ ወደ ማኅበረሰቡ እየቀረበ ያለ ሚዲያም ኾኖ ቀጥሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን