በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሚፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አስታወቁ፡፡

271

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ እና ሱዳን ወንድማማች ሕዝቦች በመሆናቸው በፍጹም ወደ ጦርነት እንደማይገቡ ዶክተር ዐብይ አህመድ አረጋግጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ እንዳመለከቱት በጣሊያን ወረራ፣ በ1977 ዓ.ም በነበረው ድርቅ፣ በቀይ ሽብር እና መሰል አስቸጋሪ ወቅቶች የሱዳን ሕዝብ ለኢትዮጵያውያን የማይረሳ ውለታ ውሏል፡፡ የሱዳን ሕዝብ የኢትዮጵያን ሕዝብ በፍጹም የመውጋት ዕቅድ እንደሌለውም አስታውቀዋል፡፡

በሱዳን በኩልም ተመሳሳይ ጥያቄ ስለሚነሳ ችግሩን በድርድር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ባስ ካለም ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ኅብረት ማምጣት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱን ሀገራት ወደ ጦርነት ለማስገባት እየሠሩ ያሉ አካላት እንዳሉም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈታና ኢትዮጵያም ሙሉ ትኩረቷን ሕዳሴ ግድብ ላይ አድርጋ እንደምትሠራም አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ዙሪያ በቅርቡ ያወጣውን ሪፖርት በተመለከተም የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚያሳስብ በመሆኑ ማጣራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ መንግሥትን የሚጠይቀው እና የሚገመግመው የስልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በየማነብርሃን ጌታቸው

Previous articleበኢትዮጵያ 136 ተጨማሪ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፡፡
Next articleከአማራ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት አምስት ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ማገገማቸውን ጤና ቢሮው ገለጸ።