አሚኮ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሲሠራ የቆየ ተቋም ነው፡፡

11
ጎንደር: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎችን ሢሠራ መቆየቱን የትምህርት ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ሚዲያው ትምህርትን ለመደገፍ እና ለማበረታታት የሠራው ሥራ ታሪክ የሚመዘግበው መኾኑንም ነው አስተያየታቸውን የሰጡ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ለአሚኮ የተናገሩት። ከአስተያየት ሰጭዎቹ መካከል የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስንታየሁ ነጋሽ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ማኅበረሰቡን ስለ ትምህርት አስፈላጊነት ግንዛቤ እንዲኖረው የተጫወተው ሚና ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል። በትምህርት ተቋማት ያሉ ችግሮችን በማሳወቅ ማኅበረሰቡ የትምህርት ተቋማትን እንዲደግፍ የሠራው ሥራ አበረታች መኾኑንም ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ራዕዩን እንዲያሳካ እና የትምህርት ሥራው የተቃና እንዲኾን እያበረከተ ላለው ተግባር ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን ትምህርት ቤቶችን በማሳየት ለሌሎች መነሻ እንዲኾን እና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ታሪክ የሚመዘግበው ሥራ ማበርከቱን በጎንደር ከተማ የአቡነ ሳሙኤል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አዩልኝ ተገኘ ተናግረዋል። አሚኮ በሰላም ቀጣናዎች ብቻ ሳይኾን አለመረጋጋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎችም የትምህርት ቤቶች እና የተማሪዎችን የመማር ማስተማር ሁኔታ ለብዙኀኑ በማሳወቅ ትልቅ ሥራ መሥራቱን ርዕሰ መምህሩ ጠቅሰዋል።
በትምህርት የተጎዳ ሀገር የማይሽር ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ በመኾኑ ችግሩን ለመሻገር ሚዲያው የትምህርቱን ዘርፍ በመደገፍ ጠንክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። አሚኮ አድማሱን እያሰፋ በሁሉም ቦታ ተደራሽ ለመኾን እየሠራ የሚገኘው የሁሉም ማኅበረሰብ ድምጽ ለመኾን ካለው ፍላጎት የተነሳ እንደኾነ የጠቀሱት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስተባባሪ ማንደፍሮ አሳየ ናቸው። በቀጣይም የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት የሕዝብ ጥያቄ የኾኑ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሻደይ በዓል ዋዜማ መከበር ጀመረ።
Next articleወድቆ የመነሳት ተምሳሌት አማራ ኤፍ ኤም ደሴ 87 ነጥብ 9 ሬዲዬ ጣቢያ።