
ሰቆጣ: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከነሐሴ 16 እስከ 21/2017 ዓ.ም ድረስ የሚከበረው የሻደይ በዓል በዋዜማውም በድምቀት መከበር ጀምሯል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አዘጋጅነት በሰቆጣ ከተማ የሚገኙ ሴት መሪዎች እና የሻደይ ተጫዋቾች በተገኙበት የሻደይ ዋዜማ እየተከበረ ነው። በማስጀመርያ መርሐ ግብሩ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልዕክት ያሥተላለፉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኀላፊ ትበርህ ታደሰ ሻደይ የሴቶችን እኩልነት የሚያሳይ ልዩ በዓል መኾኑን ተናግረዋል።
የሻደይን በዓል ስናከብር የሴቶችን መብት በማስጠበቅ ሊኾን ይገባል ያሉት ኀላፊዋ ሻደይ ከዓመት ዓመት በጉጉት የሚጠበቅ እና የሴቶች የደስታቸው ምንጭ ነው ብለዋል። የሻደይን ዋዜማ በማሥመልከት የደም ልገሳ መርሐ ግብርም እየተካሄደ ነው። በመርሐ ግብሩም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ ሴት መሪዎች ፣ የሰቆጣ ከተማ ሴቶች፣ የየወረዳ የሻደይ ተጫዋቾች ተሳታፊ ናቸው።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!