
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት አምራች እና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ ማደግ የሚቻለውም በትምህርት ነው። ለዚህም ነው ትምህርት የተለየ ትኩረት የሚያስፈልገው መኾኑ በተደጋጋሚ የሚነገረው፡፡
በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አልሄዱም፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት የተቋረጠባቸው ቦታዎችም በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል የምሥራቅ ጎጃም ዞን አንዱ ነው፡፡ በዞኑ በርካታ ትምህርት ቤቶች ላለፉት ሁለት ዓመታት አላስተማሩም። ብዛት ያላቸው ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ቆይተዋል፡፡ በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አሚኮ ያነጋገረው የአስረኛ ክፍል ተማሪ ላለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ትምህርት ቤት አለመሄዱን ተናግሯል፡፡ ትምህርት ባይቋረጥ ኖሮ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ የምገባበት ጊዜ ነበር ነው ያለው፡፡
ከትምህርት ውጭ ኾኖ ያሳለፈው ጊዜ አስቸጋሪ መኾኑን እና ስሜቱ መጎዳቱንም ገልጾልናል፡፡ ቤተሰቦቻቸው የገንዘብ አቅም ያላቸው የእድሜ አኩዮቹ ወደ ባሕር ዳር ሄደው ተምረው አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲ ሊገቡ ነው ይላል፡፡ እኔ ግን ሁለት ዓመት እድሜዬን ያለ አግባብ አባከንኩኝ ነው ያለው፡፡ አሁንም ቢኾን ግን ትምህርት ሊጀመር በመኾኑ ደስታውን ገልጿል። በሙከራ የምዝገባ ጊዜ መመዝገቡንም ተናግሯል፡፡ አሚኮ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ የሚኖሩ ወላጅ አራት ልጆቻቸው ለሁለት ዓመታት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ወደ ከተማ ልከው ለማስተማር አቅማቸው ስለማይፈቅድ ልጆቻችን ላይ ጫና አሳድሯል ብለዋል፡፡ ቤት በመዋላቸው የልጆቻቸው ጸባይ መቀየሩን እና ከቤተሰብ ጋር አለመግባበት ውስጥ እንደሚገቡም አንስተዋል፡፡
በአካባቢያቸው ትምህርት በመቋረጡ ሴት ልጆች ያለ ዕድሜያቸው መዳራቸውንም ነግረውናል፡፡ ትምህርት ለመጀመር በቀበሌያቸው በተደረገው ውይይት ወላጆች እና ተማሪዎች መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ በነበረው የሙከራ ምዝገባም ተማሪዎች በብዛት ወደ ትምህርት ቤት ሄደው መመዝገባቸውን ነው የገለጹት፡፡ ማኅበረሰቡ ትምህርት እንዲጀመር በሀገር ሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶች በኩል ያሉትን አማራጮች ሁሉ በመጠቀም ትምህርት ለማስጀመር እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መኾኑን አንስተዋል፡፡ በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህር ትምህርት በመዘጋቱ ተማሪዎች መዋያ ማጣት እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ መምህራንም ከሥራ ውጭ በመኾናቸው ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዳሳደረባቸው ነው የተናገሩት፡፡
አቅም ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ከተሞች ልከው እያስተማሩ ነው ያሉት መምህሩ የድሀ ልጆች ግን መማር አልቻሉም ነው ያሉት፡፡ ትምህርት ለመጀመር የሚደረገው እንቅስቃሴ እና የተጀመረው ምዝገባ ለተማሪዎች፣ ለወላጆች እና ለመምህራን ተስፋ የሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የትኛውም አካል ልጆች እንዲማሩ መፍቀድ እና ትምህርት ከየትኛውም ፖለቲካዊ እሳቤ ነጸ ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡
የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እናውጋው ንብረት ለ2018 የትምህርት ዘመን በወረዳው በሚገኙ 58 ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለማስጀመር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡም ልጆቹ ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው በመቆየታቸው ችግሩን ተረድቶ በሙከራ ምዝገባው በአንድ ቀን ከ1600 በላይ ተማሪዎችን መመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት። በቀጣይ ሁሉንም ተማሪዎች ለመመዝገብ የቅስቀሳ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በትምህርት ቤቶች መሟላት ያለበትን ቁሳቁስ በመለየት በማኅበረሰቡ ባለቤትነት የማሟላት እና ትምህርት ቤቶችን ዝግጁ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል። በወረዳው በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር በዕቅድ መያዙንም ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው መቆየታቸውን የተናገሩት ደግሞ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ ናቸው፡፡
በ2018 የትምህርት ዘመን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለማስጀመር የክረምት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ትምህርት ለማስጀመር ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ውይይት ተካሂዷል ነው ያሉት፡፡
“በተማሪዎች እና ወላጆቻቸው ላይ ቁጭት ተፈጥሯል” ብለዋል፡፡ ከቁጭት ባለፈም በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ነሐሴ 12/2017ዓ.ም የሙከራ ምዝገባ ተጀምሮ ውጤታማ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎችም ለመማር ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ከፍተኛ ፍላጎት እና ተነሳሽነት ታይቷል ነው ያሉት፡፡ አብዛኞቹ መምህራንም በምዝገባ ቅስቀሳ እና በትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብ ላይ እየተሳተፉ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ከሚገኙ 996 ትምህርት ቤቶች መካከል በ2017 የትምህርት ዘመን ትምህርት ሲሰጥባቸው የነበሩት 160 ትምህርት ቤቶች ብቻ መኾናቸውን አስታውሰዋል። በ2018 የትምህርት ዘመን ከ790 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ በዕቅድ ተይዟል ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ነጻ ኾነው የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ርብርብ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማሩ ምቹ ለማድረግ የማጽዳት እና ቁሳቁሶችን ለማሟላት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ከነሐሴ 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ ምዝገባ ይጀመራል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ: ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን