“የዕውቀት ዓመት ይግባ”

9
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በትምህርት ሕይወት ያለፈን ሁሉ አንድ የጋራ ጣፋጭ ትዝታ አለን። “በደህና ሁኑ፣ መለያያችን ደረሰ ቀኑ” ብለን በወርሐ ሰኔ የተሰነባበትናቸውን የትምህርት ቤት ጓደኞቻችንን እና መምህራን መስከረም ጠብቶ፣ አበቦች ፈንድተው፣ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ዳግም ስናገኛቸው ደስታችን ወደር የለውም። ፊደል ከመቁጠሩ ሌላ በለምለም የትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ መቦረቅ ልዩ የልጅነት የወል ትዝታችን ነው።
አማራ ክልል”ድንቁርና ይጥፋ፤ ዕውቀት ይስፋፋ” የሚባልበት፣ የቀለም ቀንድ የኾኑ እና ተወዳዳሪ ተማሪዎችም የሚፈልቁበት ነው። በክልሉ ውስጥ ግጭት ከተፈጠረ ወዲህ ትምህርት ታሟል። የትምህርት ቤት በሮች ተዘግተው ሚሊዮን ተማሪዎች ከዕውቀት ተነጥለው ትምህርት ቤቶቻቸውን እየናፈቁ ነው። ይባስ ብሎ አንዳንዶች ደግሞ እድሜያቸውን በማይመጥን ቦታ እና ሁኔታ ውስጥ እንደሚውሉ እየተነገረ ነው። ወላጆችም ለልጆቻቸው አዋዋል በመጨነቅ የማይገፉ የሚመስሉ ጊዜያትን እያሳለፉ ነው። የትምህርት ቤት በሮችን መከፈት የናፈቁ ተማሪዎች፣ መስከረም ጠብቶ ልጆቻችን ይማሩ ይኾን በማለት የሚጓጉ ወላጆች እልፍ ናቸው።
በሰሜን ጎጃም ዞን ጎንጅ ቆለላ ወረዳ ነዋሪ ከኾነ የተማሪ ወላጅ ጋር ቆይታ አድርጌ ነበር። ልጆችዎ ከትምህርት ተነጥለው እንዴት ከረሙ? ቀጣይስ ምን ተስፋ ይዛችኃል? ብየ ጥያቄየን ቀጠልኩ። ” አከራረሜን እነግርሃለሁ ግን ስሜን አትጥቀስብኝ” አሉኝ። ተስማማንና ቀጠሉ።
“እኔ አልተማርኩም፤ የኔ እጣ ፋንታ ልጆቸ ላይ እንዲደገም ግን በጭራሽ አልፈልግም” አሉኝ። ሁለት ልጆች አሏቸው። በ2015 ዓ.ም ትልቁ ልጃቸው 7ኛ፣ ትንሿ ደግሞ 4ኛ ክፍል እንደነበሩ አጫወቱኝ። በ2016 ዓ.ም ትምህርት ቤቶች ተዘጉ፤ እንዲከፈቱ መጠየቅም የሚያስቀጣ ኾነ። ለቀለም የሚታትሩ ተማሪዎችን እና ለዕውቀት ቀናኢ የኾኑ ወላጆችን ግጭት ካስከተለው ጭንቀት በላይ የትምህርት ቤቶች መዘጋት አንገታቸውን እንዳስደፋቸው እኒህ አባት ያስታውሳሉ። አቅም ያላቸው አንዳንድ ወላጆች ሰላም ወዳለበት አካባቢ ልጆቻቸውን በድብቅ ልከው ለማስተማር መሞከራቸውንም ነገሩን።
እርሳቸውም በቂ አቅም ባይኖራቸውም ትልቁን ልጃቸውን ቤት ተከራይተው እና ስንቅ ጭነው ወደ ባሕር ዳር ተማር ብለው ላኩት። ይህንን የሰሙ ታጣቂዎች ያዟቸው። ልጃቸውን ለማስተማር በድብቅ በመላካቸው 25 ሺህ ብር ቅጣት ተጣለባቸው፤ ልጁን መልሰው ካላመጡ ደግሞ ቅጣቱ ወደ 50 ሺህ ብር ከፍ እንደሚል ተነገራቸው። “በሬየን ከቀንበር ፈትቸ በመሸጥ 50 ሺህ ብሩን በመክፈል የልጄን ትምህርት አስቀጠልኩ በማለት መከፋታቸውን አጫወቱኝ። የ2018 መስከረም ሲጠባ ትምህርት ቤት እንደሚከፈት፣ ባሕር ዳር ያለው ልጃቸውም ተመልሶ በቀየው ኾኖ ሲማር ወጭው እንደሚቀንስላቸው እና ታናሿ ልጃቸውም ወደ ትምህርት ቤት እንደምትገባላቸው ተስፋ መሰነቃቸውን ገልጸውልኛል። ሀገር ሰላም ኾኖ ልጆች እንዲማሩ የወላጆች ሁሉ ምኞት መኾኑንም ተናግረዋል።
መነሻችንን ሰሜን ጎጃም ላይ አደረግን እንጅ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች የተዘጉ ትምህርት ቤቶች፣ ከዕውቀት የተነጠሉ ተማሪዎች እና ስለልጆቻቸው አዋዋል የሚጨነቁ ወላጆች አሉ። መሥከረም ሊጠባ ነው። ከትምህርት ገበታ ተነጥለው የቆዩ ተማሪዎች በሙሉ ወደ ትምህርት ይመለሱ ይኾን? የወላጆችስ ጭንቀት መቋጫ ያገኝ ይሆን? የትምህርት ቤት በሮች እንዲዘጉ የሚፈልጉ አካላትስ በሕጻናት ዕድሜ ላይ መጨከን መኾኑን ተረድተው ለትምህርት ተባባሪ ይኾኑ ይኾን? መሥከረም ይመልሰዋል። “የዕውቀት ዓመት ይግባ።”
በየደረጃው ያሉ የትምህርት ባለሙያዎች እና መሪዎች ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎች ይመለሱ ዘንድ እየሠሩ ነው። የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል ትምህርት መምሪያ ኀላፊ የሺወርቅ ድረስ ዞኑ በትምህርት ዘርፍ ክፉኛ ተጎድቷል፤ የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች ከዕውቀት እና ከተወዳዳሪነት ተነጥለዋል፤ ወላጆች ስለልጆቻቸው ዋጋ ከፍለዋል፤ መምህራንም ክብራቸውን ባልመጠነ መልኩ ተንገላተዋል፤ ተገድለዋልም ነው ያሉት። ትምህርት ሲቋረጥ ዕውቀት ብቻ አይደለም የሚቋረጠው ያሉት ምክትል ኅላፊዋ የልጆች ሥነ ልቦናም አብሮ እንደሚሰበር፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንደሚስፋፋ፣ ልጆች መዋል በማይገባቸው ቦታ ስለሚውሉ እና ይህም የወደፊት ሕይወታቸውን እንደሚያጨልም አብራርተዋል።
ሰው ሁሉ የተሻለ ነገን ይፈልጋል፤ የትምሕርትም ዓላማው ለሕዝብ እና ለሀገር የተሻለ ነገ መፍጠር ነው ብለዋል። በመኾኑም ማንኛውም አካል ትምህርትን መደገፍ እንጅ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥም ቢኾን እንዲዘጋ መከልከል አግባብነት የለውም ነው ያሉት።
ትምህርት ከየትኛውም አይነት ፖለቲካ መላቀቅ እና ለትውልድ መገንቢያ መኾን እንጅ ፓለቲካ እየተጫነው መጎዳት የለበትም ብለዋል። ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ሙከራም ለሕዝብ የማይጠቅም በመኾኑ መቆም እንዳለበት መክረዋል።
ወላጆች ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ በእጅጉ ይፈልጋሉ፤ ከዕውቀት የራቁ ልጆቻቸውም ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱላቸው እየጠየቁ ነው ብለዋል ምክትል መምሪያ ኀላፊዋ። ወከባ እና እንግልቱን ለሕዝብ እና ለሙያቸው ሲሉ በመቻል በሥራቸው ላይ የሚታትሩ መምህራን ነበሩ፤ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። ትምህርት ቤቶቻቸው የተዘጉባቸው መምህራን ሥራ ላይ ወደ ነበሩት ትምህርት ቤቶች በመዛወር ያስተምሩ ነበር። ይህም ታሪክ የማይረሳው የሕዝብ ውለታ መኾኑን ገልጸዋል።
እንዲህ አይነት ለትውልድ የቆሙ በርካታ ምስጉን መምህራን እንዳሉ ሁሉ በጸጥታ ችግሩ ሰበብ ሙያዊ ግዴታቸውን ወደኃላ በመተው ማድረግ የሚችሉትን ሳያደርጉ የቀሩ መምህራንም መኖራቸውን ጠቅሰዋል። እንዲህ አይነት መምህራንን በመለየት የመምከርና የማስተካከል ሥራ ማከናወናቸውንም ገልጸዋል። በ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት ሥራ ያለአንዳች መደናቀፍ እንዲካሄድ በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል። መምህራን በቂ የሥነ ልቦና ዝግጅት ኖሯቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያስችል ሥልጠና እየተሠጠ ነውም ብለዋል። በዞኑ በ2018 የትምህርት ዘመን 495 ሺህ 863 ተማሪዎችን በ503 ትምህርት ቤቶች ተመዝግበው እንዲማሩ መታቀዱንም ተናግረዋል። የትምህርት ውድቀት የሀገር እና የሕዝብን ውድቀት ያመጣል፤ ሁሉም ይህንን በውል በመረዳት ለትምህርት ውጤታማነት መሥራት አለበት ብለዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አማካሪ ካሳሁን አዳነ የክልሉ የትምህርት ሥራ የገባበት ችግር ዘርፈ ብዙ መኾኑን ገልጸዋል። ይህም ሀገራዊ ኀላፊነትን፣ ቴክኖሎጂን፣ ራዕይን እና ተልዕኮን ተሸክሞ ማሳካት የሚችል ብቁ የሰው ኃይል እያሳጣን ነው ብለዋል። የነገ ሀገራችን የዛሬ ልጆቻችንን ነው የምትመስለው የሚሉት አቶ ካሳሁን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለ ሀገር እና ስለ ሕዝብ ሲል በጋራ በመቆም ትምህርትን የሚያሰናክሉ አካሄዶችን በሙሉ እንዲታረሙ መሥራት አለበት ነው ያሉት። የክልሉ የትምህርት ከስብራት እንዲወጣ ግለሰባዊ እና ተቋማዊ ግዴታዎቻችንን መወጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን በመመዝገብ ለማስተማር ዕቅድ ተይዟልም ብለዋል። ነሐሴ 15 እና 16/2017 ዓ.ም የሙከራ ምዝገባ መርሐ ግብር ይካሄዳል፤ ከነሐሴ 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ሁሉም በክልሉ ያሉ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ ይጀምራሉ ነው ያሉት። ሁሉም ወላጆች ትምህርት ለልጆቻቸው መጻኢ እድል ወሳኝ ነገር መኾኑን በመገንዘብ ማስመዝገብ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ ነው፣ የትውልድ መገንቢያ መሣሪያ ብቻ መኾኑም በውል መታወቅ አለበት ነው ያሉት። ትምህርትን የሚያሰናክሉ አካላትም የድርጊታቸውን ውጤት በክልሉ ሕዝብ ላይ የሚያጠላውን መጥፎ ጥላ በውል ተገንዝበው መታረም አለባቸው ብለዋል። ወላጆችም የልጆች ትምህርት ቤት ለምን ይቋረጣል ብለው መሞገት እና ለመፍትሔውም መታገል እንዳለባቸው መክረዋል።
ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች በሕዝብ መገልገያ ተቋማት እና ንብረቶች ላይ ውድመት አደረሱ።
Next articleበደቡብ ወሎ ዞን የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ምዝገባ መርሐ ግብር ተጀምረ።