
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በገለጉ ከተማ በጽንፈኞች በደረሰ ድንገተኛ ወረራ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱን የወረዳው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ጽንፈኞቹ በመንግሥት ተቋማት እና በግለሰቦች ንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
በጥቃቱ 24 የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 74 ቢሮዎች ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ ሦሥት ተሽከርካሪዎች በእሳት ሲቃጠሉ አንድ ተሽከርካሪ ደግሞ ተወስዷል። የትምህርት፣ የፍትሕ፣ የጤና ጥበቃ፣ የፖሊስ እና የገንዘብ ጽሕፈት ቤቶች ከወደሙት ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ። ጥቃቱ በግለሰቦች ላይም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።። የወረዳው አሥተዳዳሪ አስማረ አንዳርጋቸው እና የሌሎች መሪዎች የቤት እቃዎቻቸውን እና የግል ንብረቶቻቸው ተዘርፈዋል።
ከወደሙት ንብረቶች መካከል የቤት እቃዎች፣ አልባሳት፣ የግል ላፕቶፖች እና ሞባይል ስልኮች ይገኙበታል። በተጨማሪም የፖሊስ አባላት የግል ንብረቶችም እንደወደሙ እና እንደተወሰዱ ተገልጿል። የቋራ ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው የጥቃቱ ዋና ዓላማ ሰዎችን መግደል፣ ማሰቃየት፣ ንብረት መዝረፍ እና የመንግሥት ተቋማትን ማውደም መኾኑን ማኅበረሰቡ ተረድቷል። ይህም በአካባቢው የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያገለግል የሕክምና አምቡላንስ ተሽከርካሪ መቃጠሉ እና መድኃኒቶች መውደማቸው ማሳያ እንደኾነ ነው የተብራራው።
ጽሕፈት ቤቱ ማኅበረሰቡ ድርጊቱን በማውገዝ እና እራሱን በመጠበቅ ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሠራ ጥሪ አቅርቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን