
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አርሶ አደሮች የጸረ ተባይ እና ጸረ አረም ኬሚካል እጥረቶች እንዳሉባቸው ተናግረዋል፡፡
በዞኑ በአንዳንድ አካባቢዎች ምርቱን ሊያበላሹ የሚችሉ ተባዮች እና አረም መከሰቱን አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል፡፡ ጥሩሀብት ነጋ የወልቃት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አርሶ አደር ናቸው፡፡ በ1ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ጥጥ፣ ሰሊጥ እና የማሽላ ሰብል እያለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የምርቱ ቁመና ሲታይ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ነው ያሉት አርሶ አደር ጥሩሀብት የጸረ ተባይ እና የአረም ማስወገጃ ኬሚካል ግብዓት እጥረት እንደገጠማቸው ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በነጋዴዎች በኩል በውድ ዋጋ መግዛታቸው ላልተገባ ወጭ እየዳረጋቸው መኾኑን ነው ያብራሩ፡፡ አርሶ አደር አሊ መሀመድ ሌላው የወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ ዞን አርሶ አደር ናቸው፡፡ 2ሺህ ሄክታር በሚደርስ መሬት አኩሪ አተር፣ ጥጥ፣ ሰሊጥ እና ማሾ እያለሙ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የአዝመራው ቁመና ሲታይ ጥሩ የሚባል መኾኑን የተናገሩት አርሶ አደር አሊ አረም በከፍተኛ ኹኔታ እንዳስቸገራቸውም ተናግረዋል፡፡ ይህንን ሊከላከሉ የሚችሉበት የጸረ-አረም ኬሚካል በመንግሥት በኩል ባለመቅረቡ ከግለሰቦች በውድ ዋጋ በመግዛት ላልተገባ ወጭ እየተዳረጉ መኾናቸውንም አብራርተዋል፡፡
ከዚህ በፊት ቀደም ብሎ በመንግሥት በኩል የጸረ አረምም ኾነ የጸረ ተባይ ኬሚካል ይቀርብላቸው እንደነበር የተናገሩት አርሶ አደር አሊ በዚህ ዓመት ምንም አይነት አቅርቦት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ድንገት እንኳን ተባይ ቢነሳ ከነጋዴ በገንዘባቸው ገዝተው የሚጠቀሙበት ጸረ ተባይ ኬሚካል አለመኖሩ የሚጠብቁትን ያክል ምርት ለማግኘት ስጋት እንደኾነባቸው ገልጸዋል፡፡ የሚመለከተው አካልም ይህንን ታሳቢ በማድረግ የጸረ አረም እና የጸረ ተባይ ኬሚካል በወቅቱ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የግብርና መምሪያ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ ኑርሁሴን አብድል ቃድር በዞኑ 561 ሺህ 856 ሄክታር መሬት ይታረሳል ተብሎ ታቅዶ 552 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡
አጠቃላይ ብቅለቱ በጥሩ ቁመና ላይ ያለ መኾኑን የተናገሩት ቡድን መሪው በአንዳንድ የእርሻ ማሳዎች ላይ ተባዮች መከሰታቸውንም አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም የጸረ ተባይ ኬሚካል በወቅቱ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡ ከዚህ በፊት በሰብሎች ላይ በወረርሽኝ መልክ ለሚነሱ የተለያዩ በሽታዎች በክልሉ እና በዞን ደረጃ የጸረ ተባይ ኬሚካል በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሮች ይቀርብ እንደነበር ያነሱት ቡድን መሪው በዚህ ዓመት ከክልልም ኾነ ከዞን ምንም አይነት ድጋፍ አለመደረጉን ተናግረዋል፡፡ በዚህም አርሶ አደሮች የጸረ ተባይ እና ጸረ አረም ኬሚካል መድኃኒት እጥረት እንደገጠመው ነው ያብራሩት፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትም አርሶ አደሮች በአካባቢው በሚገኙ ከአንድ ማዕከል የግብዓት አቅርቦት ድርጅቶች በመግዛት ተባዮችን የመከላከል ሥራ እንዲሠሩ ነው ያስገነዘቡት።
አርሶ አደሮች ያለማቋረጥ የማሳ አሰሳ እንዲያደርጉም የምክረ ሃሳብ እና ሙያዊ ድጋፍ ሥራ እየሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ ቢሮው የ2017/2018 የምርት ዘመን ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦት ስርጭቱን በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኩል እያካሄደ ይገኛል፡፡ በምርት ዘመኑ 520 ሺህ 540 ሊትር ጸረ ነፍሳት፣ ጸረ አረም እና ጸረ በሽታ ፈሳሽ ኬሚካል ለማሰራጨት ታቅዶ እስካሁን ባለው 746 ሺህ 243 ሊትር ኬሚካል ተሰራጭቷል ነው ያሉት፡፡
የጸረ ነፍሳት፣ ጸረ አረም እና ጸረ በሽታ የዱቄት ኬሚካል ደግሞ 77 ሺህ 150 ኪሎ ግራም ለማሰራጨት ታቅዶ እስካሁን ባለው 123 ሺህ 262 ኪሎ ግራም የዱቄት ኬሚካል ተሰራጭቷል ብለዋል፡፡ ይህም ከዕቅዱ አንጻር ሲታይ ስርጭቱ የተሻለ እንደኾነም ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኬሚካል በባህሪው መክረም ስለሌለበት የሚፈልገው ዞን እና ወረዳ ፍላጎቱን ለግብርና ቢሮው በማሳወቅ ፍላጎቱን መሠረት ባደረገ ፍቃድ ከግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ መውሰድ እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን