
እንጅባራ፡ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በትምህርት ዘመኑ ከ465 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር መታቀዱንም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የእቅድ ዝግጅት ቡድን መሪ ምህረት ተሠራ በትምህርት ዘመኑ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድረስ ከ465 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር መታቀዱን ተናግረዋል። በተፈጠረው ፀጥታ ችግር ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው መቆየታቸው ያነሱት አቶ ምህረት የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ለማስከፈት ከወላጆችና ከአከባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል። ዛሬ በሙከራ ደረጃ በእንጅባራና በቻግኒ ከተማ አሥተዳደሮች ስር ባሉ ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪዎች ምዝገባ ቀጣይ ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፍት ቤት ምክትል ኀላፊ ስንታየሁ የኔአባት በከተማ አሥተዳደሩ ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በሁለት ቀናት መዝግቦ ለማጠናቀቅ የሚያስች አደረጃጀት ተፈጥሮ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል። ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ የግቢ ፅዳት፣ የመማሪያ ክፍሎችና ሌሎችም አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ማስፋፊያ ግንባታና የጥገና ሥራዎች በክረምት ወራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል። ልጆቻቸውን ሲያስመዘግቡ ያገኘናቸው የተማሪ ወላጆችም የተማሪ ምዝገባ ቀድሞ መጀመሩ የትምህርት ጊዜ ብክነትን ለማስቀረት የሚያግዝ መኾኑን ተናግረዋል። ልጆቻቸውን በወቅቱ እንዳስመዘገቡ ሁሉ አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን አሟልተው በወቅቱ ለትምህርት እንደሚልኩም ገልጸዋል። በአንድ አንድ አከባቢዎች የሚስተዋለው የህፃናትን የትምህርት እድል የሚነፍግ እንቅስቃሴ ተገቢ አለመኾኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!