አሚኮ እዚህ ለመድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል።

50
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ1987 ዓ.ም ሲመሠረት በ”በኩር” ጋዜጣ የጀመረው የአማራ ማዲያ ኮርፖሬሽን እነኾ ሥሦት አስር ዓመታትን አስቆጥሯል።
በ30 ዓመታት ጉዞ ከበኩር ጋዜጣ ባለፈ በቴሌቪዥን፣ በሬድዮ፣ በኤፍ ኤም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ዘመን በወለደው ዲጂታል ሚዲያ በመላው ዓለም ለሚገኙ አድማጭ፣ ተመልካቹ እና አንባቢያን መረጃዎችን እየመገበ ይገኛል። ሚዲያው ከጀመረ ጀምሮ አሁን ከደረሰበት ደረጃ የደረሰው እንዲሁ አልጋ ባልጋ ሳይኾን በርካታ ፈተናዎችን በመጋፈጥ እንደኾነ መሥራች የነበሩት ጋዜጠኞች ይናገራሉ። ካነጋገርናቸው መሥራች ጋዜጠኞች መካከል ጋዜጠኛ መቅጫ እንግዳየሁ አንዱ ናቸው። የቀድሞው ጋዜጠኛ መቅጫ እንግዳዬሁ ከመምህርነት ሥራ ነበር በደብረ ታቦር የዜና ወኪልነት ተቀጥረው መሥራት የጀመሩት።
ጋዜጠኛው እንደገለጹት በወቅቱ በኪራይ ቤት፣ በድንጋይ እና እንጨት ላይ ጭምር ተቀምጦ ዘገባ መሥራት የተለመደ ነበር። ከነበረው የመሠረተ ልማት እና የትራንስፖርት ችግር በበቅሎ እና በእግር በመጓዝ መዘገብ ሌላኛው ፈተና ነበር ብለዋል። በየደረጃው የተቀመጡ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ስለሚዲያ ምንነት ከነበራቸው ግንዛቤ አኳያ መረጃ ለማግኘት ፈታኝ ነበር ይላሉ። በወቅቱ የነበሩ ሠራተኞች ይህንን ሁሉ ችግር ተቋቁመው የክልሉን ባሕል እና ወግ ለማስተዋወቅ፣ የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብት እንዲጠናከር ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል።
ከሠሯቸው ሥራዎች መካከል የአውራንባ ማኅበረሰብ የሥራ ባሕል፣ ወግ፣ እሴት እና የአካባቢ አሥተዳደር ሥርዓት ላይ የተሠራው ዝግጅት ተጠቃሽ ነው። በጋዜጠኛው የተሠራውን ዝግጅት ተከትሎ በአሚኮ ወደ ሰባት የሚኾኑ ዘጋቢ ፊልሞች፣ በውጭ ሀገር ጋዜጦች እና መጽሔቶች፣ በዩኒቨርሲታዎች ጭምር ተደጋጋሚ ጥናቶች ተደርገው በመላው ዓለም እንዲታወቅ ተደርጓል ብለዋል። በተሠራው ሥራ የማኅበረሰቡ የሥራ ባሕል ለሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ምሳሌ መኾን መቻሉን ገልጸዋል። በአጎራባች በሚገኙ አካባቢዎች በሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ግጭት እንዲቀንስ፣ የሥራ ባሕል እንዲጎለብት መሠረት መኾናቸውን ነው የገለጹት።
አሁን ላይም ባለሙያው ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጅዎች ፈጥኖ በመላመድ፣ በዕቅድ ላይ በመመሥረት፣ ተቋማዊ ተግባቦትን በማጠናከር፣ በሥልጠና እና በትምህርት ራስን በማብቃት ማኅበረሰቡን ማገልገል ይገባል ብለዋል። ሌላኛው መሥራች ጋዜጠኞች መካከል እና አሁን ላይ በጡረታ ላይ የሚገኙት ጋዜጠኛ ይገርማል አማረ ይገኙበታል። በወቅቱ በትንሽ እና በቂ ወንበር እንኳ በሌለበት ቢሮ፣ እንደ አሁኑ በተሽከርካሪ ሳይኾን በበቅሎ ጭምር ተጉዘው ይሠሩ እንደነበር አሥታውሰዋል። ውሎ እና አዳራቸውም በአርሶ አደሮች ቀዬ እንደነበር ገልጸዋል።
በወቅቱ ይጠቀሟቸው የነበሩ የሚዲያ መሳሪያዎች የዘመኑ ባለመኾናቸው ዘገባዎችን ለመሥራት ሌላው ፈተና እንደነበር ነው የገለጹት። ይሁን እንጅ በነበረው ተቋማዊ አንድነት የማኅበረሠቡን ባሕል እና ወግ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ተችሏል። አሁን ላይ አሚኮ የታጠቃቸው ዘመናዊ የሚዲያ መሳሪያዎች፣ በዞኖች የከፈታቸው ማሠራጫ ጣብያዎች ካለው የሰው ኀይል ጋር ተዳምሮ የዘገባ ሥርጭቱን በፍትሐዊነት ተደራሽ ለማድረግ አቅም እንደሚኾን ነው የገለጹት። ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጅዎች ቀድሞ ተላምዶ መተግበር፣ ራስን ማብቃት እና በዕቅድ መምራትን ባሕል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ለሚዲያው መጠናከር ከተቋሙ ሠራተኞች ባለፈ ልምዳቸውን እና ዕውቀታቸውን ያካፈሉ አካላት ሚናቸው ከፍተኛ እንደነበርም ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleከ6ሺህ በላይ ተማሪዎችን በፓይለት ምዝገባ ሂደት ለመመዝገብ ማቀዱን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።
Next articleበአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ተጀምሯል።