ከ6ሺህ በላይ ተማሪዎችን በፓይለት ምዝገባ ሂደት ለመመዝገብ ማቀዱን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።

8
ወልድያ: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የ2018 የትምህርት ዘመን የፓይለት ምዝገባ ጀምሯል።
በምዝገባ ሂደቱ ላይ አሚኮ ያገኛቸው የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በክረምት ወቅት የተሻለ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ነግረውናል። በምዝገባ ሂደቱ ጓደኞቻቸውን በማግኘታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ተማሪዎቹ በትምህርት ዘመኑ ከመምህራን እና ከሚወዱት የትምህርት ገበታ እስኪገናኙ መቸኮላቸውንም ነው ያስረዱት። የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አበበ ደምሴ በሁለቱ ቀናት ሙሉ በሙሉ ምዝገባ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ተስፋማርያም ይመር ምዝገባው ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም እና ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የሚቆይ እንደኾነም ነው የጠቆሙት። ሦሥት የአንደኛ ደረጃ እና አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለፓይለት ምዝገባ ተመርጠው ምዝገባው እየተካሄደ ነው ብለዋል። በቅደመ መደበኛ እና በአንደኛ ደረጃ ብቻ ከ6ሺህ 600 በላይ ተማሪዎችን በሁለት ቀናት ለመመዝገብ መታቀዱንም አስገንዝበዋል። ምዝገባው በስኬት አንዲጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክርን ጨምሮ የተሟላ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተወካይ ኀላፊው ነግረውናል። ከፓይለት ምዝገባው በኋላ ጥንካሬ እና ድክመትን በመለየት በሁሉም ትምህርት ቤቶች እስከ ነሐሴ መጨረሻ ምዝገባ የሚደረግ መኾኑን ጠቁመዋል። ተወካይ ኀላፊው በትምህርት ዘመኑ በአጠቃላይ 25 ሺህ 404 ተማሪዎችን በመመዝገብ ትምህርት ለማስጀመር ጥረት ይደረጋልም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleሰላም እና እርቅ ለማወረድ አባታዊ ኃላፊነታቸዉን በመወጣት ላይ የነበሩ አባት በታጣቂዎች መገደላቸውን የአማራ ክልል ሰላም ካውንስል ገለጸ።
Next articleአሚኮ እዚህ ለመድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል።